Wednesday, February 5, 2020


ጉረኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች
በመጨረሻዎቹ ቀናት ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን እንደሚመጣ ይህን እወቅ። ምክንያቱም ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብ የሚወዱ፣ ጉረኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ታማኝ ያልሆኑ፣ ተፈጥሯዊ ፍቅር የሌላቸው፣ ለመስማማት ፈቃደኞች ያልሆኑ፣ ስም አጥፊዎች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ ጥሩ ነገር የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ግትሮች፣ በኩራት የተወጠሩ፣ ከአምላክ ይልቅ ሥጋዊ ደስታን የሚወዱ ይሆናሉ፤ ለአምላክ ያደሩ መስለው ይታያሉ፤ በሥራቸው ግን ኃይሉን ይክዳሉ።”2 ጢሞ. 3:1-5
መጽሐፍ ቅዱስ ከላይ የተጠቀስውን ህሳቤ እያስተማረ እያለ፣በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ጉረኝነትን እንደ ጥሩ ነገር አድርገው ይዘውታል። ጠንካራ ጎኔ፣ ችሎታዬና ያከናወንኩት ጥሩ ሥራ ይታይልኝ ማለት የተለመደ እየሆነ መጥቷል። አንዳንዶች አሸናፊ ለመሆን ጉራ መንዛት ያስፈልጋል ብለው ያምናሉ። ጉረኝነት የአንድን ሰው ክብር ከፍ እንደሚያደርግ የሚሰማቸውም አልታጡም። ታይም መጽሔትትሕትና ጊዜ ያለፈበት እየሆነ መጥቷልሲል ጽፏል። ጁዲ ጌሊን የተባሉ ደራሲ እንደሚከተለው ብለዋል:- “የሚያሳዝነው ግን ያለምንም እፍረት ጉራ መንዛት . . . አዲስ ፋሽን ሆኗል። ከጓደኛ ወይም ከሚያውቁት ሰው ጋር በሚደረገው ጭውውት ውስጥ ጉራ መንፋት እንደ ቅመም ይጨመራል።
ብዙዎች ተደናቂ የሆኑ ሰዎችን እንደ አርአያ አድርገው በመመልከት የሚያደርጉትን ሁሉ ይቀዳሉ።በዚህ የታሪክ ወቅት ላይ የእኔ በዓለም ላይ ታላቅ ሰው መሆን እንዲሁ በአጋጣሚ የመጣ አይደለምሲል አንድ የቀድሞ የቦክስ ሻምፒዮና የተናገራቸውን ቃላት ሰምተህ ይሆናል። የቢትልስ የሙዚቃ ባንድ አባል የሆነ አንድ ሰውበአሁኑ ጊዜ እኛ ከኢየሱስ ክርስቶስ የበለጠ ተወዳጅነት አለንሲል የተናገረው የታወቀ አባባልም አለ። አንዳንዶች እነዚህን አባባሎች ክፋት እንደሌለባቸው አድርገው ቢመለከቷቸውም ሌሎች ግን ራስን ከፍ ከፍ ማድርግ ተገቢ መሆኑን የሚያሳዩ ጥሩ ምሳሌዎች እንደሆኑ አድርገው በመመልከት እነዚህን ቃላት የተናገሩትን ሰዎች ይከተላሉ።
የጉረኝነት መብዛት የሚከተለውን ጥያቄ ያስነሣል:- አንድ ሰው ስለ ንብረቱና ስለ ችሎታው ጉራውን ቢነዛ ትክክል ነውን? አንድ ሰው በሥራው ውጤት ኩራት ቢሰማውና ይህንንም ለቅርብ ጓደኞቹና ለዘመዶቹ ቢነግር ምንም ስሕተት የለበትም። ይሁን እንጂአንድ ዓይነት ሀብት ወይም ችሎታ ካለህ በሌሎች ዘንድ እንዲታይልህ አድርግበሚለው አባባል ስለሚስማሙት ሰዎች ምን ሊባል ይቻላል? በተጨማሪም በግልጽ ጉራቸውን ባይነዙም በተዘዋዋሪ ግን ስለችሎታቸውና ስላከናወኑት ሥራ ሌሎች እንዲያውቁላቸው ለማድረግ ስለሚጥሩትስ? አንዳንዶች እንደሚሉት እንዲህ ዓይነቱ ልታወቅ ልታወቅ ባይነት ትክክል ወይም አስፈላጊ ነውን?
ሰዎች ጉራ መንዛታቸው በአንተ ላይ የሚኖረውን ተጽዕኖ አስብ። ለምሳሌ ቀጥሎ ያሉትን አነጋገሮች እንዴት ትመለከታቸዋለህ?
ሌሎች ሰዎች ከጻፏቸው መጽሐፎች ይልቅ እኔ ያልጻፍኳቸው መጽሐፎች ይበልጣሉ።” — አንድ የታወቁ ደራሲ።
በፍጥረት ጊዜ ኖሬ ቢሆን ኖሮ አጽናፈ ዓለም የተሻለ አቀማመጥ እንዲኖረው ጠቃሚ ምክር እሰጥ ነበር።” - አንድ የመካከለኛው ዘመን ንጉሥ።
አምላክ ሊኖር አይችልም፤ ምክንያቱም አምላክ ካለ ከኔ በቀር ሌላ ሊሆን አይችልም።” — አንድ 19ኛው መቶ ዘመን ፈላስፋ። በዚህ አነጋገራቸው እነዚህ ሰዎች ይማርኩሃልን? አብረሃቸው ብትሆን የምትደሰት ይመስልሃልን? እንደማትደሰት የተረጋገጠ ነው። በቅንነትም ሆነ በቀልድ የሚነገር ጉራ ሌሎች እንዲጨነቁ፣ እንዲናደዱ፣ ምናልባትም ቅንዓት እንዲያድርባቸው ያደርጋል። በመዝሙራዊው አሳፍ ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ ይህ ነበር። እሱምየኃጢአተኞችን ሰላም አይቼ በዓመጸኞች ቀንቼ ነበርናሲል ሳይሸሽግ ተናግሯል። (መዝሙር 73:3) ማናችንም ብንሆን በወዳጆቻችንና አብረውን በሚውሉ ሰዎች ላይ መጥፎ ስሜት ማሳደር እንደማንፈልግ የተረጋገጠ ነው። አንደኛ ቆሮንቶስ 13:4 “ፍቅር . . . አይመካምይላል። አምላካዊ የሆነ ፍቅርና ለሌሎች ስሜት ያለን አሳቢነት ችሎታችንና ሀብታችን ይታይልን ከማለት እንድንቆጠብ ይገፋፋናል።
አንድ ሰው ራሱን የሚቆጣጠርና የማይመካ ከሆነ አጠገቡ ያሉት ሰዎች እንዲዝናኑና ስለራሳቸው ጥሩ ስሜት እንዲኖራቸው ያደርጋል። ይህ ደግሞ እጅግ ውድ የሆነ ችሎታ ነው። እንግሊዛዊ የፖለቲካ ሰው የነበሩት ሎርድ ቼስተርፊልድከቻልክ ከሌሎች ሰዎች የበለጠ ጥበበኛ ሁን፤ ነገር ግን ከእነሱ የበለጠ ጥበበኛ መሆንህን አትንገራቸውሲሉ ልጃቸውን የመከሩት ምናልባት ይህን በአእምሮአቸው ይዘው ይሆናል።
የሰዎች ተሰጥዎ ይለያያል። ለአንዱ ቀላል የሆነው ለሌላው ከባድ ሊሆን ይችላል። አንድ ሰው ፍቅር ካለው የእሱ ዓይነት ተሰጥዎ የሌላቸውን ሰዎች በርኅራኄ እንዲይዝ ይገፋፋዋል። ሌላው ሰው ደግሞ በሌላ መስክ የራሱ ተሰጥዎ ሊኖረው ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስእግዚአብሔር ለእያንዳንዱ የእምነትን መጠን እንዳካፈለው፣ እንደ ባለ አእምሮ እንዲያስብ እንጂ ማሰብ ከሚገባው አልፎ በትዕቢት እንዳያስብ በመካከላችሁ ላለው ለእያንዳንዱ በተሰጠኝ ጸጋ እናገራለሁሲል መክሮናል።  ሮሜ 12:3
አንዳንድ ሰዎች ከጉረኛ ሰዎች ጋር በሚሆኑበት ጊዜ የበታችነት ስለሚሰማቸው ከእነሱ ይርቃሉ። ሌሎች ደግሞ ከዚህ የተለየ ግምት ይወስዳሉ። ጉረኞች በራሳቸው የማይተማመኑ ሰዎች ናቸው ብለው ይደመድማሉ። ፍራንክ ትሪፔት የተባሉት ደራሲ ጉረኛ ሰው በሌሎች ዓይን ለምን ዝቅ ብሎ እንደሚታይ እንደሚከተለው በማለት ያብራራሉ:- “ጉረኝነት ብዙውን ጊዜ አንዳንድ የግል ድክመቶችን እንደሚያሳይ ማንም ሰው በልቡ ያውቃል።ብዙ ሰዎች የጉረኞች ውስጣዊ ሁኔታ በቀላሉ ስለሚገባቸው ጉራ ከመንዛት መቆጠብ ጥበብ አይደለምን?
ግን እኮ ሊካድ አይችልም!”
አንዳንዶች ራስን ከፍ ከፍ ማድረግ ተገቢ እንደሆነ ለማስመሰል የሚሰጡት ምክንያት ይህ ነው። በአንዳንድ ነገሮች በእርግጥ ተሰጥዎ እያላቸው እንደሌላቸው ሆኖ መታየት ግብዝነት እንደሆነ ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ ጉራቸው እውነት ነውን? ለራስ የሚሰጠው ግምት ከአድልዎ የጸዳ አይሆንም። እኛ ለራሳችን እንደ ትልቅ ችሎታ አድርገን የምንገምተው ነገር በሌሎች ዘንድ ተራ ሊሆን ይችላል። አንድ ሰው ችሎታውን ማሳየት እንዳለበት በኃይል ከተሰማው ችሎታው ያን ያህል እንዳልሆነ፤ የማስታወቂያ ድጋፍ የሚያስፈልገው ደካማ ችሎታ መሆኑን ያሳያል። መጽሐፍ ቅዱስእንደ ቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅየሚል ማስጠንቀቂያ በመስጠት ራስን የማታለል ሰብዓዊ ዝንባሌ እንዳለ ይጠቁማል።  1 ቆሮንቶስ 10:12
አንድ ሰው በአንድ ዓይነት መስክ ልዩ ተሰጥዎ ቢኖረውም እንኳ ይህ ራሱ ጉራውን እንዲነዛ ሊያደርገው ይገባልን? አይገባም፤ ምክንያቱም ጉራ መንዛት ሰውን ከፍ ከፍ ያደርጋል፤ ነገር ግን ያለን ማንኛውም ተሰጥዎ ከአምላክ የመጣ ነው። ክብር ሊቀበል የሚገባው እርሱ ነው። በተፈጥሮ ላገኘነው ነገር ለምን ክብር እንቀበላለን? (1 ቆሮንቶስ 4:7) ከዚህም በተጨማሪ ጠንካራ ጎኖች እንዳሉን ሁሉ ድክመቶችም አሉን። ሐቀኝነት ስህተቶቻችንንና ድክመቶቻችንን እንድናውቅ ያስገድደናልን? እንዲህ ብለው የሚያስቡ ጉረኞች የሉም ማለት ይቻላል። ንጉሥ ሄሮድስ አግሪጳ ግሩም የንግግር ችሎታ ያለው ሰው ኖሮ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ከትምክህተኝነት አለመራቁ መጥፎ አሟሟት አስከትሎበታል። በሄሮድስ ላይ የደረሰው ይህ አስቀያሚ ሁኔታ ትምክህተኝነት በብዙ ሰዎች ዘንድ የተጠላ እንደሆነ ሁሉ በአምላክ ዘንድም የቱን ያህል የተጠላ እንደሆነ ያሳያል።  የሐዋ. ሥራ 12:21–23
ተሰጥዎቻችንና ጠንካራ ጎኖቻችን ምንም ማስታወቂያ ሳንናገር ራሳቸው መታወቃቸው አይቀርም። ሌሎች ሰዎች አንድ ሰው ያለውን ችሎታ ወይም ያከናወነውን ጥሩ ሥራ ተመልክተው ሲያመሰግኑት ምስጋናውን ለሚቀበለው ሰው የበለጠ ሞገስ ይሆንለታል። ምሳሌ 27:2 “ሌላ ያመስግንህ እንጂ አፍህ አይደለም፤ ባዕድ ሰው እንጂ ከንፈርህ አይደለምበማለት የጥበብ ምክር ይሰጣል።
አንዳንዶች ፉክክር ባለበት በዛሬው ኅብረተሰብ ውስጥ ተወዳዳሪን ለማሸነፍ በትምክህት ራስን ከፍ ከፍ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ስለ ችሎታዎቻቸው በይፋ ካልተናገሩና እንታይ እንታይ ካላሉ ሳይደነቁና ማንም ሳያውቃቸው ተረስተው የሚቀሩ ስለሚመስላቸው ይጨነቃሉ። ቮግ ከተባለው መጽሔት የተወሰደው የሚከተለው አስተያየት የእነሱን ዓይነት ጭንቀት የሚያሳይ ነው:- “ድሮ ትሕትና ጥሩ ሥነ ምግባር እንደሆነ እንማር ነበር፤ አሁን ግን ዝምተኝነት ጉድለት እንዳለብን ሊያስቆጥረን እንደሚችል እየተማርን ነው።
የዚህን ዓለም መመዘኛ ተከትለው ለመሻሻል ለሚፈልጉ ሰዎች ይህ ዓይነቱ ጭንቀት ምናልባት ተገቢ ሊሆን ይችላል። ሆኖም አንድ ክርስቲያን የሚኖረው አቋም ከዚህ የተለየ ነው። አንድ ክርስቲያን አምላክ ትዕቢተኛ ያልሆኑትን ትሑታን ሰዎች እንደሚፈልግና በችሎታቸውም እንደሚጠቀም ያውቃል። ስለዚህ አንድ ክርስቲያን በራስ ወዳድነት ዘዴዎች መጠቀም የለበትም። እርግጥ ነው፣ ከመጠን በላይ በራሱ የሚመካ ግለሰብ ተከራክሮ ወይም አግባብቶ ጊዜያዊ ክብር ሊያገኝ ይችል ይሆናል። ውሎ አድሮ ግን ይጋለጣል፣ ትሑት መሆንን ይማራል ወይም ውርደት ይደርስባታል። ኢየሱስ ክርስቶስራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳል፣ ራሱንም የሚያዋርድ ሁሉ ከፍ ይላልሲል እንደተናገረው ነው።  ማቴዎስ 23:12 ምሳሌ 8:13 ሉቃስ 9:48
አንድ ደራሲ  “የማገኘው ማንኛውም ሰው በሆነ መንገድ ይበልጠኛል፤ ምክንያቱም ከእርሱ የምማረው ነገር ይኖራልሲሉ ጽፈዋል። የእርሳቸው አነጋገርለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳን አታድርጉ፣ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቁጠርከሚለው ጳውሎስ በመለኮታዊ መንፈስ አነሣሽነት ለክርስቲያኖች ከጻፈው ምክር ጋር ይስማማል። (ፊልጵስዩስ 2:3) በዚህ ዓይነት አቅምንና ቦታን ማወቅ አንድን ሰው ከሌሎች እንዲማር ያደርገዋል።
ስለዚህ ጠንካራ ጎንህ ደካማ ጎንህን የሚያሳይ እንዳይሆን ተጠንቀቅ። ጉራ ችሎታህንና ያከናወንካቸውን መልካም ሥራዎች እንዲያቃልልብህ አትፍቀድ። ባሉህ ባሕርያት ላይ አቅምንና ቦታን የማወቅን ግሩም ባሕርይ አክልባቸው። አንድ ሰው በሌሎች ሰዎች ፊት ከፍ ብሎ እንዲታይ የሚያደርገው ይህ ነው። አቅምንና ቦታን ማወቅ አንድ ሰው ከሌሎች ሰዎች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረው ይረዳዋል፤ እንዲሁም በእግዚአብሄር ዘንድ ተቀባይነት ያስገኝለታል።  ሚክያስ 6:8 2 ቆሮንቶስ 10:18
በመጨረሻው ቀን ሰዎችትምክህተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎችይሆናሉ። እነዚህ ሦስት ባሕርያት አንድ ባይሆኑም ሁሉም ከኩራት ጋር ይዛመዳሉ። የመጀመሪያው ባሕርይትምክህተኝነትነው። አንድ መዝገበ ቃላት እንደሚናገረው እዚህ ላይ ትርጉሙከሚገባ በላይ ራስን ከፍ ከፍ ማድረግወይምማድረግ የማይችለውን አደርጋለሁ ብሎ ተስፋ መስጠትማለት ነው። ስለዚህ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች እዚህ ላይጉረኞችየሚለውን ቃል ለምን እንደሚጠቀሙ ሊገባን ይችላል። ቀጥሎ የተጠቀሰውትዕቢተኞችወይም ቃል በቃል ሲተረጎምከሌላው የሚበልጡ መስለው የሚታዩየሚለው ነው። በመጨረሻ የተጠቀሰውተሳዳቢዎችነው። ተሳዳቢዎች ሲባል እግዚአብሄር ስለሚያዋርዱ ወይም እግዚአብሄር ላይ መጥፎ ቃል ስለሚናገሩ ሰዎች ብቻ መናገሩ ነው ብለው የሚያስቡ ሰዎች ይኖሩ ይሆናል። ይሁን እንጂ ቃሉ በሰዎች ላይ ጎጂ፣ አዋራጅ ወይም የስድብ ቃል የሚናገሩትንም ይጨምራል። ስለዚህ ጳውሎስ የተናገረው አምላክንም ሆነ ሰዎችን ስለሚሳደቡ ሰዎች ነው።
የትዕቢተኛ ስው ባህሪ
በንቀት ላይ የተመሠረተ ኩራት፣ የበላይነት ስሜት፣ እብሪትን ያካትታል፣ ትዕቢት የትሕትና ተቃራኒ ነው።ትዕቢትእናትዕቢተኛተብለው የተተረጎሙት የግሪክኛና የዕብራይስጥ ቃላትትልቅከፍተኛእናየበላይመስሎ መታየት የሚል ትርጉም አላቸው። ትዕቢተኛ የሆነ ሰው ከሌሎች ሰዎች ሁሉ የበላይ ወይም ከፍ ያለ እንደሆነ ይሰማዋል። በመሆኑም እንዲህ ያለው ሰው ብዙውን ጊዜ ከተገቢው በላይ ክብርና ትኩረት እንዲሰጠው ይፈልጋል፤ ሌሎችን በንቀት የሚመለከት ከመሆኑም በላይ አክብሮት በጎደለው መንገድ ይይዛቸዋል።
ትዕቢት ከአስተሳሰብ ጋር ብቻ የተያያዘ መጥፎ ባሕርይ አይደለም። ኢየሱስ ክርስቶስ ትዕቢትን ከግድያ፣ ከሌብነት፣ ከስድብና ከሌሎች ክፉ ድርጊቶች ጋር የፈረጀው ሲሆን እንደነዚህ ያሉት ነገሮችከውስጥ ይኸውም ከሰው ልብእንደሚወጡ ተናግሯል። (ማር 7:21, 22) የኢየሱስ እናት የሆነችው ማርያምበልባቸው ሐሳብ ትዕቢተኛ የሆኑትንም በትኗቸዋልበማለት ስለ ይሖዋ ተናግራለች። (ሉቃስ 1:51) ዳዊትምልቤ አይኩራራምበማለት ወደ ይሖዋ ጸልዮአል። መዝ 131:1 ኢሳ 9:9 ዳን 5:20
እግዚአብሄር በትሕትና ሲያገለግል የቆየ ሰው እንኳ ሀብት ወይም ሥልጣን በማግኘቱ አሊያም በቁንጅናው፣ ባገኘው ስኬት፣ በጥበቡ ወይም ከሌሎች በሚያገኘው ሙገሳ ምክንያት ትዕቢተኛ ሊሆን ይችላል። የይሁዳው ንጉሥ ዖዝያ በዚህ ረገድ ምሳሌ ይሆነናል። ለበርካታ ዓመታት ሕዝቡን በጥሩ ሁኔታ ሲያስተዳድር እግዚአብሄር በረከት አግኝቶ ነበር። (2ዜና 26:3-5) መጽሐፍ ቅዱስ ከጊዜ በኋላ የሆነውን ሲናገር እንዲህ ይላል፦ይሁን እንጂ ዖዝያ በበረታ ጊዜ ለጥፋት እስኪዳረግ ድረስ ልቡ ታበየ፤ በዕጣን መሠዊያው ላይ ዕጣን ለማጠን ወደ እግዚአብሄር ቤተ መቅደስ በመግባት በአምላኩ እግዚአብሄር ላይ ታማኝነት የጎደለው ድርጊት ፈጸመ።” (2ዜና 26:16) ዖዝያ በትዕቢት ተነሳስቶ አምላክ ለእስራኤል ነገሥታት ፈጽሞ የከለከለውን የክህነት ሥራ ለማከናወን ሞክሯል፤ አምላክ ግን የንግሥናና የክህነት ሥራን ለያይቶ አስቀምጧል።
ጥሩ ንጉሥ የነበረው ሕዝቅያስም በአንድ ወቅት ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ልቡ ታብዮ ነበር፤ ይህ ባሕርይ ወደሚገዛው ሕዝብም ተጋብቶ እንደነበር ጥርጥር የለውም። ሕዝቅያስ ስኬታማ መሆን የቻለው እግዚአብሄር ስለባረከው ነበር፤ ይሁን እንጂ እግዚአብሄር ላደረገለት ነገር አድናቆት ማሳየትም ሆነ ለዚያ ሁሉ መመስገን ያለበት እግዚአብሄር እንደሆነ መቀበል አቃተው። ፀሐፊው ስለ እርሱ ሲጽፍ እንዲህ ብሏል፦ይሁንና ሕዝቅያስ ልቡ ታብዮ ስለነበር ለተደረገለት መልካም ነገር አድናቆት ሳያሳይ ቀረ፤ እግዚአብሄር ቁጣ በእሱ፣ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ መጣ።ደስ የሚለው ግን ይህን አደገኛ ዝንባሌ አስወግዷል። ዘገባው በመቀጠል እንዲህ ይላል፦ይሁን እንጂ ሕዝቅያስ ስለ ልቡ ትዕቢት ራሱን ዝቅ አደረገ፤ እሱና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ትሕትና አሳዩ፤ እግዚአብሄር ቁጣ በሕዝቅያስ ዘመን አልመጣባቸውም።”2ዜና 32:25, 26 ከኢሳ 3:16-24 እና ሕዝ 28:2, 5, 17 ጋር አወዳድር።
እግዚአብሄር ትዕቢተኞችን ይቃወማል። ትዕቢተኛ ሰዎች በቅን ሰዎች የሚጠሉ ቢሆንም ከዚህ የሚከፋው እግዚአብሄር አምላክ የሚቃወማቸው መሆኑ ነው። (ያዕ 4:6 1ጴጥ 5:5) ትዕቢት ሞኝነትና ኃጢአት ነው (ምሳሌ 14:3 21:4) እግዚአብሄር ትዕቢተኞችን ይቃወማል እንዲሁም ዝቅ ያደርጋቸዋል። (2ሳሙ 22:28 ኢዮብ 10:16 40:11 መዝ 18:27 31:18, 23 ኢሳ 2:11, 17) አንድ ሰው የትዕቢት ባሕርይውን ማስወገድ ካልቻለ ጥፋት ያስከትልበታል። እግዚአብሄር በሕዝቦቹ ላይ በትዕቢት የተነሳው የጥንቱ የሞዓብ ብሔር ድምጥማጡ ጠፍቷል። (ኢሳ 16:6 25:10, 11 ኤር 48:29) አሥሩን ነገድ ያቀፈው የእስራኤል መንግሥት እንኳ በልቡ በታበየና እብሪተኛ በሆነ ጊዜ ከቅጣት አላመለጠም።ኢሳ 9:8-12
አንድ ሰው በልቡ ውስጥ ትዕቢት እንዳይኖር መጠንቀቅ ይኖርበታል። በተለይ የሚያደርጋቸው ነገሮች ሲሳኩለት ወይም ከፍ ያለ ቦታ ወይም ኃላፊነት ሲሰጠው መጠንቀቅ ይኖርበታል።ኩራት ጥፋትን፣ የትዕቢት መንፈስም ውድቀትንእንደሚቀድም መዘንጋት አይኖርበትም። (ምሳሌ 16:18) በውስጡ ትዕቢት እንዲያድግ ከፈቀደ ይህ ባሕርይ ሙሉ በሙሉ ሊቆጣጠረውና እግዚአብሄር ተቀባይነት ለሌለው አስተሳሰብ አሳልፎ ከሚሰጣቸው ብሎም ሞት ይገባቸዋል ከሚላቸው ሰዎች ተርታ እንዲመደብ ሊያደርገው ይችላል። (ሮሜ 1:28, 30, 32) እንዲህ ያለው ማስጠንቀቂያ በተለይ በእነዚህበመጨረሻዎቹ ቀናትመሰጠቱ በጣም አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱ ለመቋቋም አስቸጋሪ በሆነው በዚህ ዘመን ሰዎች ትዕቢተኞች እንደሚሆኑ አስቀድሞ ተነግሯል።2ጢሞ 3:1, 2

በተጨማሪም የአምላክን ሞገስ ማግኘት የሚፈልግ ሰው ሌሎች የትዕቢት መንፈስ እንዲያድርባቸው ከሚያደርገው ባሕርይ ይኸውም ከሽንገላ መራቅ ይኖርበታል። የምሳሌ መጽሐፍባልንጀራውን የሚሸነግል ሰው፣ ለእግሩ ወጥመድ ይዘረጋበታልይላል። (ምሳሌ 29:5) አንድ ሰው ሌሎችን የሚሸነግል ከሆነ በባልንጀራው ላይ ጥፋት ከማስከተሉም በላይ (“የሚሸነግል አንደበትም ጥፋት ያስከትላል ምሳሌ 26:28) እሱ ራሱ የአምላክን ሞገስ ያጣል። ሐዋርያው ጳውሎስ ከሽንገላ እና ከትዕቢት ለመራቅ ጥረት አድርጓል።1ተሰ 2:5, 6


0 comments:

Post a Comment