Monday, December 3, 2018

ወላጆችእናቤተሰቦች


ልጅ ማለት ብዙ ተባዙ ከሚለው አምላካዊ ቃል ትዕዛዝ የሚገኝ የእግዚአብሔር በረከት ነው። ቅዱስ ዳዊት “ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታዎች ናችው”(መዝ 126፥3) እንዳለ።
ልጅ ሰው እራሱን ተክቶ የሚያልፍበት ልዩ አምላካዊ መንገድ ነው።

ልጆችን ተንከባክቦ የማሳደግ አስፈላጊነት

አንድ ሰው በሕፃንነቱ የተማራቸው ወይም ሳይማር ያለፋቸው ነገሮች ወደፊት በሚኖሩት ችሎታዎች ላይ ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ። ታዲያ ልጆች የተሟላ እድገት ያላቸውና የተሳካላቸው ሰዎች እንዲሆኑ ከወላጆቻቸው ማግኘት የሚያስፈልጋቸው ነገር ምንድን ነው? አንዳንዶች በቅርብ አሥርተ ዓመታት የተደረጉ ምርምሮችን መሠረት በማድረግ የደረሱበትን ድምዳሜ ተመልከት።
የአንጎል ነርቮች መገናኛዎች ወይም ሲናፕስስ
የሳይንስ ሊቃውንት የአንጎልን አሠራር በምስል ለመቅረጽ የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች እየተሻሻሉና እየተራቀቁ በመምጣታቸው የአንጎልን የእድገት ሂደት በይበልጥ ለማጥናት ችለዋል። እነዚህ ጥናቶች መረጃዎችን ማመዛዘን፣ ስሜቶችን ተገቢ በሆኑ መንገዶች መግለጽና አንደበተ ርቱዕ መሆን የሚያስችሉትን የአንጎል አሠራሮች ለማዳበር የአንድ ሕፃን የጨቅላነት ዕድሜ ወሳኝነት እንዳለው አረጋግጠዋል። ኔሽን መጽሔት “የአንጎል መዋቅር፣ በዘር ውርስ በሚገኙ መረጃዎችና በአካባቢያዊ ተጽዕኖዎች መካከል በየጊዜው በሚኖረው መስተጋብር በሚቀረጽበት የመጀመሪያዎቹ ዓመታት የአንጎል ነርቭ አውታሮች በጣም ከፍተኛ በሆነ ፍጥነት ይዘረጋሉ” ይላል።
ከእነዚህ ሲናፕስስ ተብለው ከሚጠሩት የነርቭ መገናኛዎች አብዛኞቹ የሚፈጠሩት አንድ ሕፃን በተወለደ ጥቂት ዓመታት ውስጥ እንደሆነ ሳይንቲስቶች ያምናሉ። የሕፃናት አስተዳደግ ባለሞያ የሆኑት ዶክተር ቤሪ ብሬዘልተን እንደሚሉት “ከማስተዋል፣ ራስን ከማወቅና ሌሎችን ከማመን ችሎታ እንዲሁም ከመማር ፍላጎት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው የሕፃን ልጅ የነርቭ አውታር የሚቀረጸው” በዚህ ጊዜ ነው።
የአንድ ሕፃን አንጎል በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ዓመታት ውስጥ በመጠን፣ በነርቭ አውታሮች መዋቅርና በሚያከናውነው ተግባር በሚያስደንቅ ፍጥነት ያድጋል። ሕፃኑ ለአእምሮ እድገት በሚያመችና ብዙ ትምህርት በሚያገኝበት አካባቢ ከኖረ የሲናፕስስ ግንኙነቶች በጣም ይበራከቱና በአንጎል ውስጥ እጅግ ብዙ የነርቭ አውታር መሥመሮች ይፈጠራሉ። ማሰብ፣ መማርና ማገናዘብ የሚያስችሉት እነዚህ የነርቭ አውታሮች ናቸው።
የአንድ ሕፃን አንጎል የሚያገኘው ማነቃቂያ በበዛ መጠን መሥራት የሚጀምሩት የነርቭ ሴሎች ብዛትና በሴሎቹ መካከል የሚፈጠረው መተሳሰር የዚያኑ ያህል ይጨምራል። ይህ ማነቃቂያ እንደ ቁጥርና ቋንቋ በመሰሉት ትምህርቶች ብቻ የሚመጣ አለመሆኑን ማወቅ ተገቢ ነው። ሳይንቲስቶች ስሜታዊ ማነቃቂያም እንደሚያስፈልግ ተገንዝበዋል። ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ያልታቀፉ፣ ያልተሻሹና ሰዎች ያላጫወቷቸው ልጆች የሚኖሯቸው የሲናፕስስ ግንኙነቶች አነስተኛ ናቸው።
ሕፃናት እያደጉ ሲሄዱ በአንጎል ውስጥ አረም የማረም ዓይነት ሂደት ይካሄዳል። ሰውነት አስፈላጊ ያልሆኑ የሲናፕስስ መሥመሮችን ያስወግዳል። ይህ ደግሞ አንድ ልጅ በሚኖረው ሊዳብር የሚችል ችሎታ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። የአንጎል ተመራማሪ የሆኑት  እንደሚሉት “አንድ ሕፃን ትክክለኛውን ዓይነት ማነቃቂያ በትክክለኛው ዕድሜ ላይ ካላገኘ የነርቭ አውታሮቹ በትክክል ሊያድጉ አይችሉም።” በዚህም ምክንያት የልጁ የመማር፣ የመናገርና ቁጥሮችን የማስላት ችሎታ ዝቅተኛ ሊሆን እንዲሁም ትልቅ ሰው በሚሆንበት ጊዜ ከጤናና ከባሕርይ ጋር የተያያዙ ችግሮች ሊያጋጥሙት ይችላሉ።  ስለዚህ አንድ ሰው ሕፃን በነበረበት ጊዜ ያጋጠሙት ሁኔታዎች ትልቅ ሰው ሲሆን በሚኖረው ሕይወት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። ሰውየው መንፈሰ ጠንካራ ወይም ደካማ፣ ለሰው አዛኝ ወይም ጨካኝ፣ አርቆ አሳቢ ወይም ጠባብ አእምሮ ያለው መሆኑ ሕፃን ሳለ ባጋጠሙት ነገሮች ላይ ሊመካ ይችላል። ስለዚህ ወላጆች የሚኖራቸው ሚና ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው። አንድ የሕፃናት ሐኪም “ከእነዚህ የልጅነት ገጠመኞች መካከል በጣም ወሳኝ የሆነው አሳቢና አስተዋይ የሆነ አሳዳጊ ወላጅ ማግኘት ነው” ብለዋል። ይህ በጣም ቀላል ሊመስል ይችላል። ልጆቻችሁን በእንክብካቤ ብታሳድጓቸው ወደፊት የተሳካ ሕይወት ይኖራቸዋል። ይሁን እንጂ ለልጆች ተገቢውን እንክብካቤ መስጠት ቀላል ነገር እንዳልሆነ ወላጆች ያውቃሉ።
አንድ ጥናት እንዳመለከተው ጥያቄ ከቀረበላቸው ወላጆች መካከል 25 በመቶ የሚሆኑት ልጃቸውን የሚያሳድጉበት መንገድ የመማር ችሎታውን፣ በራስ የመተማመን መንፈሱንና የመማር ፍላጎቱን ሊያዳብርለት ወይም ሊያዳክምበት እንደሚችል አያውቁም። ይህ ደግሞ የልጃችሁን የተፈጥሮ ችሎታ ማዳበር የሚቻልበት ጥሩ መንገድ ምንድን ነው? አመቺ የሆነ ሁኔታ ሊፈጠርለት የሚችለው እንዴት ነው? የሚሉትን ጥያቄዎች ያስነሳል።

መጽሐፍ ቅዱስ ልጆችህን ለማሰልጠን
ልጆችን ማሳደግም  ከባድና ጥረት የሚጠይቅ ሲሆን ከፍተኛ ጥንቃቄም ይሻል። ከዚህ አኳያ አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸውን እንዴት አድርገው ቢያሳድጉ እንደሚሳካላቸው ግራ ቢገባቸው ብዙም አያስገርምም። በርካታ ወላጆችም የሚረዳቸው ቢያገኙ ደስ ይላቸዋል። እያንዳንዱ ወላጅ ከሁሉ የተሻለውን መመሪያ ማግኘት እንደሚፈልግ ግልጽ ነው። ታዲያ እንዲህ ያለውን መመሪያ ከየት ማግኘት ይቻላል? መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ልጆች አስተዳደግ መመሪያ ለመስጠት የተጻፈ መጽሐፍ ባይሆንም ፈጣሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎችን በመንፈሱ አነሳስቶ በዚህ ጉዳይ ላይ በጣም ጠቃሚ የሆነ ምክር እንዲጽፉ አድርጓል። መጽሐፍ ቅዱስ መልካም ባሕርያትን በልጆች ውስጥ የመቅረጽን አስፈላጊነት የሚያጎላ ሲሆን ብዙ ሰዎች ይህ እምብዛም ትኩረት እንዳልተሰጠው ይሰማቸዋል። (ኤፌሶን 4:22-24) በዚህ ረገድ ልጆች ሊያገኙት ከሚገባው ሥልጠና ውስጥ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ወሳኝ ድርሻ አለው። በተለያዩ ዘመናት የኖሩና የተለያዩ ባሕሎች ያሏቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ይህን ምክር ተግባራዊ በማድረጋቸው ተጠቅመዋል። ስለዚህ እናንተም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ምክር በሥራ ላይ በማዋል ልጆቻችሁን በማሰልጠን ረገድ ስኬታማ መሆን ትችላላችሁ።
የወላጆች አርዓያነት—የላቀ የማስተማሪያ ዘዴ
“እንግዲህ አንተ ሌሎችን የምታስተምር፣ ራስህን አታስተምርምን? አትስረቅ ብለህ የምትሰብክ፣ ትሰርቃለህን? አንተ ሰዎች ማመንዘር የለባቸውም የምትል፣ ታመነዝራለህን?”—ሮሜ 2:21, 22
ልጆችን ለማስተማር ከሁሉ የተሻለው ዘዴ በቃልም ሆነ በድርጊት ምሳሌ መሆን ነው። ወላጆች በአነጋገርም ሆነ በምግባር ጥሩ አርዓያ ሳይሆኑ ለልጃቸው ትምህርት እንስጥ ቢሉ ልጁ ግብዝ እንደሆኑ አድርጎ ለመመልከት ጊዜ አይፈጅበትም። የሚያስተምሩት ነገር ሁሉ ዋጋ ያጣል። ለምሳሌ ወላጆች ልጆቻቸውን ስለ ሐቀኝነት ማስተማር ከፈለጉ እነርሱም ሐቀኞች መሆን አለባቸው። አንዳንድ ወላጆች ስልክ ሲደወልላቸው ለማነጋገር ካልፈለጉ ልጃቸው “የለም (የለችም)” ብሎ እንዲመልስ ማድረጋቸው የተለመደ ነው። እንዲህ ዓይነት መመሪያ የተሰጠው ልጅ መጀመሪያ ላይ ሊጨንቀውና ግራ ሊጋባ ይችላል። እየዋለ እያደር ግን እሱም አስቸጋሪ ሁኔታ ሲያጋጥመው ብዙም ሳይሳቀቅ መዋሸት ይጀምራል። ስለዚህ ወላጆች ልጃቸው ሐቀኛ ሆኖ እንዲያድግ ከፈለጉ እነርሱ ራሳቸው በቃላትም ሆነ በድርጊት ሐቀኛ መሆን አለባቸው።
ልጃችሁ የታረመ አነጋገር እንዲኖረው ማሰልጠን ትፈልጋላችሁ? እንግዲያው በዚህም ምሳሌ መሆን ይኖርባችኋል። ልጃችሁ እናንተን ለመማር ፈጣን ነው። አንድ አባት እንዲህ ይላል:- “እኔና ባለቤቴ በንግግራችን ውስጥ ጸያፍ ቃላትን ላለመጠቀም ወስነናል። እርስ በርስ የምንከባበር ከመሆኑም በላይ ስንቆጣ ወይም ስንናደድ እንኳን እየተጯጯህን አንነጋገርም። በቃላት ከማስተማር ይልቅ ምሳሌ መሆንን ይበልጥ ውጤታማ ሆኖ አግኝተነዋል። ልጆቻችን ሌሎችን የሚያነጋግሩት በአክብሮትና በትሕትና እንደሆነ ስንመለከት ደስ ይለናል።” መጽሐፍ ቅዱስ በገላትያ 6:7 ላይ “ሰው የሚዘራውን ያንኑ ያጭዳል” ይላል። ልጆቻቸው የላቀ የሥነ ምግባር አቋም እንዲኖራቸው የሚፈልጉ ወላጆች እነርሱ ራሳቸው በእነዚህ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች መመራት አለባቸው።
ከልጆቻችሁ ጋር የማውራት ልማድ ይኑራችሁ
“ለልጆችህም [የአምላክን ሕግጋት] አስጠናቸው፤ በቤትህ ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛና ስትነሣም ስለ እነርሱ ተናገር።”—ዘዳግም 6:7
ከተለመደው የሥራ ሰዓት በተጨማሪ የመሥራት ልማድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ ነው። ባልም ሆነ ሚስት የሚሠሩ ከሆነ ደግሞ በልጆቹ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አለው። ብዙ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር የሚያሳልፉት ጊዜ እየቀነሰ ነው። እቤት ካሉም የቤት ውስጥ ሥራዎችን ወይም ሌሎች ተግባራትን ማከናወን ስለሚኖርባቸው ሊደክማቸው እንደሚችል የታወቀ ነው። እንዲህ ባለ ሁኔታ ከልጆቻችሁ ጋር ልብ ለልብ ለማውራት ጊዜ ማግኘት የምትችሉት እንዴት ነው? ከልጆቻችሁ ጋር አብራችሁ የቤት ውስጥ ሥራዎችን የምታከናውኑ ከሆነ ለዚህ የሚሆን ጊዜ ማግኘት ትችላላችሁ። አንድ የቤተሰብ ራስ ከልጆቹ ጋር ለማውራት የሚችልበት ጊዜ ለማግኘት ሲል ቴሌቪዥኑን ከቤት እስከ ማስወጣት ደርሷል። እንዲህ ብሏል:- “መጀመሪያ ላይ ልጆቹ ብዙም ደስ አላላቸውም ነበር። ሆኖም አንዳንድ አእምሮን የሚያመራምሩ ጨዋታዎችን ሳጫውታቸውና ከመጻሕፍት ያነበብኳቸውን ደስ የሚሉ ታሪኮች ስነግራቸው ቀስ በቀስ እየለመዱት ሄዱ።”
ልጆች ገና ከሕፃንነታቸው አንስቶ ከወላጆቻቸው ጋር በግልጽ መነጋገር ቢለምዱ ጥሩ ነው። አለበለዚያ በጉርምስና ዕድሜያቸው ላይ ችግር ሲያጋጥማቸው ወላጆቻቸውን ችግራቸውን ሊያወያዩአቸው እንደሚችሉ የቅርብ ጓደኞች አድርገው አይመለከቷቸውም። የልባቸውን ሳይደብቁ እንዲነግሯችሁ ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው? ምሳሌ 20:5 እንዲህ ይላል:- “የሰው ልብ ሐሳብ እንደ ጥልቅ ውሃ ነው፤ አስተዋይ ሰው ግን ከዚያ ቀድቶ ያወጣዋል።” ወላጆች “ምን ይመስልሃል?” እንደሚሉ ያሉ የአመለካከት ጥያቄዎችን በመጠቀም ልጆቻቸው ሐሳባቸውንና ስሜታቸውን እንዲገልጹ ማበረታታት ይችላሉ።
ልጃችሁ ከባድ ጥፋት ቢያጠፋ ምን ታደርጋላችሁ? በደግነት ልትረዱት የሚገባው በዚህ ጊዜ ነው። ጥፋቱን ሲናገር ስሜታችሁን ተቆጣጥራችሁ ለማዳመጥ ሞክሩ። አንድ አባት እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲከሰት ምን እንደሚያደርግ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ልጆቼ ጥፋት ሲሰሩ ከሚገባው በላይ ላለመቆጣት እሞክራለሁ። ቁጭ ብዬ የሚሉትን በጥሞና አዳምጣለሁ። እንዲሁም የተፈጸመውን ሁኔታ በሚገባ ለማገናዘብ እጥራለሁ። ስሜቴን መቆጣጠር ካቃተኝ ለተወሰነ ጊዜ ዝም በማለት ራሴን አረጋጋለሁ።” ስሜታችሁን ተቆጣጥራችሁ የምታዳምጡ ከሆነ ልጆቻችሁ የምትሰጧቸውን እርማት ለመቀበል ይበልጥ ቀላል ይሆንላቸዋል።
በፍቅር ላይ የተመሠረተ ተግሣጽ ያስፈልጋል
“አባቶች ሆይ፤ እናንተም ልጆቻችሁን አታስቆጧቸው፤ ነገር ግን በጌታ ምክርና ተግሣጽ አሳድጓቸው።”—ኤፌሶን 6:4። ልጆቻችሁን በማሰልጠን ረገድ ውጤታማ መሆን እንድትችሉ ተግሣጽ የምትሰጡበት መንገድ ወሳኝነት አለው። ወላጆች ልጆቻቸውን ‘ሊያስቆጧቸው’ የሚችሉት እንዴት ነው? ተግሣጹ ከተሠራው ጥፋት ጋር የማይመጣጠን ከሆነ ወይም ከልክ በላይ በነቀፋ ላይ ያተኮረ ከሆነ ልጆች እልኸኛ ይሆናሉ። ተግሣጽ ምንጊዜም ቢሆን በፍቅር መሰጠት ይኖርበታል። (ምሳሌ 13:24) በምክንያት የምታስረዷቸው ከሆነ ተግሣጽ የምትሰጧቸው ስለምትወዷቸው እንደሆነ ይገነዘባሉ።—ምሳሌ 22:15፤ 29:19። በሌላ በኩል ተገቢ ያልሆነ ነገር ማድረግ የሚያስከትለውን መጥፎ ውጤት ልጁ እንዲያየው ማድረጉ ጥሩ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ልጁ በሌላ ሰው ላይ ተገቢ ያልሆነ ነገር ካደረገ ሄዶ ይቅርታ እንዲጠይቅ ማድረግ አለባችሁ። የቤተሰቡን መመሪያዎች ከጣሰ እነዚህን መመሪያዎች መጠበቅ ያለውን አስፈላጊነት ለማስገንዘብ በአንዳንድ መብቶቹ ላይ ማዕቀብ ሊደረግበት ይችላል።
በተገቢው ጊዜ ተግሣጽ መስጠቱ የሚበረታታ ነው። መክብብ 8:11 እንዲህ ይላል:- “በወንጀል ላይ ባፋጣኝ ፍርድ ካልተሰጠ፣ የሰዎች ልብ ክፉን በማድረግ ዕቅድ ይሞላል።” ብዙ ልጆች ማድረግ የሌለባቸውን ነገር ካደረጉ በኋላ ከቅጣት ለማምለጥ ይችሉ እንደሆነ ለማየት ይፈልጋሉ። በመሆኑም ጥፋት ካጠፉ እንደሚቀጡ ካስጠነቀቃችኋቸው እንደተናገራችሁት ከማድረግ ወደ ኋላ አትበሉ።
ጥሩ መዝናኛ ጠቀሜታ አለው
“ለመሣቅም ጊዜ አለው፤ . . . ለጭፈራም ጊዜ አለው።”—መክብብ 3:4
አንድ ልጅ በአዕምሮም ሆነ በአካል እያደገ እንዲሄድ የጨዋታ ጊዜና ሚዛኑን የጠበቀ ጤናማ መዝናኛ ያስፈልገዋል። ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር አብረው የሚዝናኑ ከሆነ በቤተሰቡ መካከል ያለው ትስስር የሚጠናከር ከመሆኑም በላይ ልጆቹም የሚያስብላቸው እንዳለ ስለሚሰማቸው ተረጋግተው ያድጋሉ። የቤተሰቡ አባላት ሊሳተፉባቸው የሚችሉ መዝናኛዎች የትኞቹ ናቸው? ጊዜ ወስዳችሁ ካሰባችሁበት ልታደርጓቸው የምትችሏቸው በርካታ አስደሳች ነገሮች አሉ። ለምሳሌ ብስክሌት መንዳት ወይም እንደ ቴኒስና ቮሊ ቦል ያሉ ጨዋታዎችን መጫወት ይቻላል። እንዲሁም የሙዚቃ መሣሪያዎችን አብሮ በመጫወት ምን ዓይነት አስደሳች ጊዜ ማሳለፍ እንደሚቻል አስቡት። ተፈጥሮን ለማድነቅ በአቅራቢያችሁ ያሉ ቦታዎችን በመጎብኘትም ግሩም ትዝታዎችን መፍጠር ይቻላል።
ወላጆች እንዲህ ያሉ አጋጣሚዎችን በመጠቀም ልጆቻቸው ለመዝናኛ ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖራቸው ሊያደርጉ ይችላሉ። ሦስት ወንዶች ልጆች ያሉት አንድ ክርስቲያን አባት እንዲህ ብሏል:- “በተቻለኝ መጠን ልጆቼ ሲጫወቱ አብሬያቸው ለመጫወት እሞክራለሁ። ለምሳሌ ያህል፣ የኮምፒዩተር ጨዋታዎችን ሲጫወቱ ስለ ጨዋታው እጠይቃቸዋለሁ። በጋለ ስሜት ስለ ጨዋታው ሲነግሩኝ አጋጣሚውን በመጠቀም ጥሩ ያልሆነ መዝናኛ ያለውን አደጋ እነግራቸዋለሁ። ተገቢ ያልሆኑ መዝናኛዎችን እንደሚያስወግዱ አስተውያለሁ።” አዎን፣ ከቤተሰባቸው ጋር በሚያሳልፉት የመዝናኛ እንቅስቃሴ የሚረኩ ልጆች ዓመጽን፣ የሥነ ምግባር ብልግናንና አደገኛ ዕፅ መውሰድን የሚያሳዩ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን፣ የቪዲዮ ፊልሞችንና የኢንተርኔት ጨዋታዎችን ወደ መመልከት አያዘነብሉም።
ልጆቻችሁ ጥሩ ጓደኞች እንዲያፈሩ እርዷቸው
“ከጠቢብ ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የተላሎች ባልንጀራ ግን ጉዳት ያገኘዋል።”—ምሳሌ 13:20
አራት ልጆቹን በተሳካ ሁኔታ ያሳደገ አንድ አባት እንዲህ ይላል:- “የልጆቻችሁ የጓደኛ ምርጫ በጣም ወሳኝ ነው ቢባል ተጋንኗል ሊባል አይችልም። ስትገነቡ የኖራችሁትን ሁሉ አንድ መጥፎ ጓደኛ ሊንደው ይችላል።” ይህ አባት ልጆቹ ጥሩ ጓደኞች እንዲያፈሩ ለመርዳት የቅርብ ጓደኛዬ የምትለው ማን ነው? እርሱን የመረጥከው ለምንድን ነው? ከእርሱ መኮረጅ የምትፈልገው ምንድን ነው? እንደሚሉ ያሉ ጥያቄዎችን በዘዴ ይጠይቃቸዋል። አንድ ሌላ ወላጅ ደግሞ ልጆቹ የቅርብ ጓደኞቻቸውን እቤት እንዲጋብዟቸው ያደርጋል። ከዚያም ምን ዓይነት ጓደኞች እንደሆኑ ይመለከትና ለልጆቹ ተገቢውን ምክር ይሰጣቸዋል።
ልጆች ከእኩዮቻቸው ጋር ብቻ ሳይሆን በዕድሜ ከሚበልጧቸው ትላልቅ ሰዎችም ጋር ጓደኝነት መመሥረት እንደሚችሉ ማስተማርም ጠቃሚ ነው። የሦስት ወንዶች ልጆች አባት የሆነው በምሰን እንዲህ ይላል:- “በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተጠቀሱት እንደ ዳዊትና እንደ ዮናታን ሁሉ ጓደኛ ሲባል የግድ የዕድሜ እኩያ መሆን እንደሌለበት ልጆቼ እንዲገነዘቡ አደርጋለሁ። እንዲያውም የተለያየ ዕድሜ ያላቸውን ክርስቲያኖች ከልጆቼ ጋር እንዲጫወቱ እጋብዛቸዋለሁ። በመሆኑም ልጆቼ የዕድሜ እኩዮቻቸው ካልሆኑ ከተለያዩ ሰዎች ጋር ይቀራረባሉ።” ልጆች አርዓያ ከሚሆኑ አዋቂዎች ጋር መቀራረባቸው ብዙ ነገር መማር የሚችሉበት አጋጣሚ ይከፍትላቸዋል።
ልጆቻችሁን በማሰልጠን ረገድ ሊሳካላችሁ ይችላል
በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የተካሄደ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው ልጆቻቸው ራስን መግዛት፣ ሐቀኝነትና ራስን መገሰጽ የመሳሰሉ ባሕርያትን እንዲያዳብሩ የሚጥሩ በርካታ ወላጆች ብዙ ጊዜ አይሳካላቸውም። ለምን? በጥናቱ ላይ የተሳተፈች አንዲት እናት እንዲህ ብላለች:- ‘የሚያሳዝነው ልጆቻችሁን ከመጥፎ ነገሮች ለመጠበቅ ያለው ብቸኛው አማራጭ በቤት ውስጥ ዘግታችሁባቸው ከውጪው ዓለም ጋር እንዳይገናኙ ማድረግ ነው።’ ይህቺ እናት እንዲህ ያለችው ልጆች የሚያድጉበት ዓለም ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እየተበላሸ መሄዱን አስባ ነው። ታዲያ በዚህ ሁኔታ ልጆችን በተሳካ ሁኔታ ማሳደግ ይቻላል?

ስለ ሰው አፈጣጠር ከማንም በላይ የሚያውቀው እግዚአብሄር የልጆች አስተዳደግን በሚመለከት ከሁሉ የተሻለውን ምክር ሰጥቶናል። “ልጅን የሚሄድበትን መንገድ አስተምረው፤ በሚሸመግልበት ጊዜ ከዚያ ፈቀቅ አይልም” ብሎናል። (ምሳሌ 22:6) ልጆቻችሁን በመጽሐፍ ቅዱስ ምክር መሠረት ካሰለጠናችኋቸው ካደጉ በኋላ ኃላፊነት የሚሰማቸው፣ ለሌሎች የሚያስቡና መልካም ሥነ ምግባር ያላቸው ሲሆኑ የመመልከት አስደሳች አጋጣሚ ታገኛላችሁ። በዚህም በሰዎች ብቻ ሳይሆን በሰማይ ባለው አባታችን በእግዚአብሄር ዘንድ የሚወደዱ ይሆናሉ።

0 comments:

Post a Comment