Friday, March 22, 2019


 ቁጡ የሆኑ ሰዎች የበዙት ለምንድን ነው?
ለቁጣ መንስኤ የሚሆኑት ነገሮች ውስብስብ ናቸው። የሳይንስ ሊቃውንትም እንኳ ስለ ቁጣ ያላቸው ግንዛቤ አነስተኛ እንደሆነ አይሸሽጉም። ይሁን እንጂ ሁላችንም “የሚያስቆጣ ነገር” ሲያጋጥመን ልንበሳጭ እንደምንችል በአእምሮ ጤንነት መስክ የተሰማሩ አብዛኞቹ ባለሙያዎች የሚስማሙበት ነገር ነው።
የሚያስቆጣ ነገር የሚባለው አንድን ሰው የሚያናድድ ወይም የሚያበሳጭ ነገር ነው። ብዙውን ጊዜ የምንናደደው የፍትሕ መጓደል ወይም መድልዎ ሲፈጸም ስንመለከት ነው። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሌሎች እንደናቁን ሆኖ ሲሰማን ለምሳሌ ስንሰደብ ወይም ክብራችንን ዝቅ የሚያደርግ ነገር ሲያጋጥመን ልንቆጣ እንችላለን። ሥልጣናችን ወይም መልካም ስማችን እንደተነካ ሲሰማንም በቁጣ ልንገነፍል እንችላለን።
እርግጥ ነው፣ ሰዎችን የሚያስቆጧቸው ነገሮች የተለያዩ ናቸው። ዕድሜና ፆታ ሌላው ቀርቶ ባሕል እንኳ ሰዎችን የሚያስቆጧቸው ነገሮች እንዲለያዩ ሊያደርጉ ይችላሉ። ከዚህም በላይ ሰዎች የሚያስቆጡ ነገሮች ሲያጋጥሟቸው ስሜታቸውን የሚገልጹበት መንገድም ይለያያል። አንዳንድ ሰዎች ብዙም የማይቆጡ ሲሆን ከተቆጡም ነገሩን ቶሎ ይረሱታል፤ ሌሎች ግን በቀላሉ የሚቆጡ ከመሆናቸውም በላይ ቁጣቸው እስኪበርድ ቀናት፣ ሳምንታት፣ ወራት ወይም ከዚያ የሚበልጥ ጊዜ ሊፈጅ ይችላል።
በዓለም ላይ ሊያስቆጡን የሚችሉ ብዙ ነገሮች አሉ። በዚህ ላይ ደግሞ ሰዎች ከበፊቱ የበለጠ በቀላሉ የሚቆጡ እየሆኑ መጥተዋል። ለምን? አንዱ ምክንያት በዘመናችን የተስፋፋው ለሰዎች አሳቢነት አለማሳየትና እኔ ልቅደም የሚል መንፈስ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “በመጨረሻዎቹ ቀኖች . . . ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብ የሚወዱ፣ ጉረኞች፣ ትዕቢተኞች፣ . . . ግትሮች፣ በኩራት የተወጠሩ” እንደሚሆኑ ይናገራል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) እነዚህ ቃላት በዛሬው ጊዜ ያሉትን የአብዛኞቹን ሰዎች ዝንባሌ በትክክል የሚገልጹ አይደሉም?  በእርግጥም ራስ ወዳድ የሆኑ ሰዎች የፈለጉትን ነገር ማግኘት ካልቻሉ ብዙውን ጊዜ ውጤቱ ቁጣ ነው። ቁጣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የሚሄድ ችግር እንዲሆን ያደረጉ ሌሎች በርካታ ምክንያቶችም አሉ።
የወላጆች ምሳሌነት
ወላጆች፣ ልጆቻቸው በልጅነትና በጉርምስና ዕድሜያቸው በሚያዳብሩት ባሕርይ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። የሥነ ልቦና ተመራማሪ የሆኑት ሃሪ ሚልዝ “ሰዎች ቁጣቸውን መግለጽ የሚማሩት ገና ከትንሽነታቸው ጀምሮ በአካባቢያቸው ሌሎች ቁጣቸውን የሚገልጹበትን መንገድ በመኮረጅ ነው” በማለት ተናግረዋል።
አንድ ሕፃን ብስጩ ሰዎች በበዙበት አካባቢ ካደገ በሌላ አባባል ሰዎች በትንሽ በትልቁ በቁጣ ሲገነፍሉ የሚያይ ከሆነ በሕይወቱ ውስጥ ችግር ባጋጠመው ቁጥር በቁጣ ምላሽ እንዲሰጥ እየሠለጠነ ነው ሊባል ይችላል። የልጁን ሁኔታ የተበከለ ውኃ ከሚጠጣ ተክል ጋር ልናመሳስለው እንችላለን። በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ያለ ተክል ቢያድግም እድገቱ ሊቀጭጭና ምናልባትም ዘላቂ ጉዳት ሊደርስበት ይችላል። ቁጣም እንደተበከለ ውኃ ነው፤ እንዲህ ባለ አካባቢ ያደጉ ልጆች ትልልቅ ሰዎች ሲሆኑ ቁጡ የመሆን አጋጣሚያቸው ሰፊ ነው።
በ1800 ከዓለም ሕዝብ መካከል በከተሞች ውስጥ የሚኖረው 3 በመቶ ገደማ ነበር። በ2008 ግን ይህ ቁጥር አድጎ 50 በመቶ የደረሰ ሲሆን በ2050 ደግሞ 70 በመቶ እንደሚደርስ ይጠበቃል። ቁጥራቸው እየጨመረ የሚሄድ ሰዎች በተጨናነቁ ከተሞች ውስጥ ተፋፍገው መኖር በቀጠሉ መጠን ቁጡና ብስጩ የሆኑ ሰዎች እየበዙ መሄዳቸው የማይቀር ነው። ሜክሲኮ ሲቲን እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ በምድር ላይ ካሉት ትልቅና እጅግ የተጨናነቁ ከተሞች አንዷ በሆነችው በዚህች ከተማ ዋነኛው የውጥረት መንስኤ የትራፊክ መጨናነቅ ነው። አንድ ጋዜጠኛ እንደዘገበው ሜክሲኮ ሲቲ 18 ሚሊዮን የሚያህል ሕዝብና ስድስት ሚሊዮን መኪኖች ያሉባት ከተማ በመሆኗ “በዓለም ላይ ካሉት ዋና ከተሞች ሁሉ ይበልጥ ውጥረት የነገሠባት ሳትሆን አትቀርም።” ይኸው ጋዜጠኛ አክሎም “ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ በመኖሩ ሰዎች በቁጣ የመገንፈላቸው አጋጣሚ በጣም ከፍ ያለ ነው” ብሏል።
በሕዝብ የተጨናነቁ ከተሞች በሌሎች መንገዶችም ውጥረት ያስከትላሉ፤ ከእነዚህም መካከል የአየር ብክለት፣ ከፍተኛ መጠን ያላቸውና የሚረብሹ ድምፆች መበራከት፣ የመኖሪያ ቤት እጦት፣ የባሕል ልዩነትና የወንጀል ድርጊቶች መበራከት ይገኙበታል። ውጥረት የሚያስከትሉ ነገሮች በበዙ ቁጥር ሰዎች የመበሳጨት፣ የመቆጣትና ትዕግሥት የማጣት አዝማሚያቸው እየጨመረ ይሄዳል።
ኢኮኖሚው የሚያስከትለው ውጥረት በዓለም ላይ የሚታየው የኢኮኖሚ ውድቀት በየትኛውም ቦታ በሚኖሩ ሰዎች ላይ ውጥረትና ጭንቀት አስከትሏል። ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም እና የተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት (አይ ኤል ኦ) በ2010 በጋራ ያወጡት አንድ መግለጫ እንደሚያሳየው “በመላው ዓለም ከ210 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ሥራ አጥ እንደሆኑ ይገመታል።” የሚያሳዝነው ነገር፣ ከሥራ ከተቀነሱት ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ተቀማጭ ገንዘብ የሌላቸው ሲሆን ለሥራ አጦች የሚሰጥ እርዳታም አያገኙም።
ሥራ ያላቸው ሰዎችም ቢሆኑ መጨነቃቸው አይቀርም። አይ ኤል ኦ እንደገለጸው ከሥራ ጋር ተያይዞ የሚመጣ ውጥረት “ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ” ሆኗል። በኦንታሪዮ፣ ካናዳ የአስተዳደር አማካሪ የሆኑት ሎርን ከርቲስ “ሰዎች ሥራቸውን እንዳያጡ የሚፈሩ ሲሆን የሚታያቸው መጥፎ መጥፎው ነገር ነው” በማለት ይናገራሉ፤ “እንዲህ ዓይነት ስጋት ስላላቸው ከአለቆቻቸው ወይም ከሌሎች ሠራተኞች ጋር ሙግት መግጠም ይቀናቸዋል” በማለት አክለው ተናግረዋል።
የሩጫ ውድድር ላይ እንደሆንክና የምትሮጠው እግሮችህ በሰንሰለት ታስረው እንደሆነ አድርገህ አስብ፤ ይሁንና በሰንሰለት የታሰርከው አንተ ብቻ መሆንህን ብታውቅ ምን ይሰማሃል? በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በዘራቸው ወይም በሌላ ምክንያት መድልዎ ሲደርስባቸው የሚሰማቸው ስሜት ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው። ሰዎች ሥራ፣ ትምህርት፣ መኖሪያ ቤትና ሌሎችም ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን እንዳያገኙ መድልዎ ሲደረግባቸው ይበሳጫሉ።
ሌሎች ኢፍትሐዊ ድርጊቶችም የአንድን ሰው መንፈስ ሊደቁሱና ከፍተኛ የስሜት ሥቃይ ሊያስከትሉበት ይችላሉ። የሚያሳዝነው ነገር አብዛኞቻችን በሕይወታችን ውስጥ በሆነ ወቅት ላይ የፍትሕ መጓደል ደርሶብን ያውቃል። ከሦስት ሺህ ከሚበልጡ ዓመታት በፊት ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን “የተገፉትን ሰዎች እንባ ተመለከትሁ፤ የሚያጽናናቸውም አልነበረም” በማለት ተናግሮ ነበር። (መክብብ 4:1) የፍትሕ መጓደል ሲስፋፋና የሚያጽናና ሲጠፋ አንድ ሰው ልቡ በቁጣ ሊሞላ ይችላል።
በቴሌቪዥንና በሌሎችም የመገናኛ ብዙኃን የሚታየው ዓመፅ በልጆች ላይ ምን ተጽዕኖ እንዳለው ለማወቅ ከአንድ ሺህ በላይ የሚሆኑ ጥናቶች ተደርገዋል። በመገናኛ ብዙኃን የሚቀርቡትን ነገሮች በተመለከተ ለሰዎች መረጃ የሚሰጥ አንድ ድርጅት መሥራች የሆኑት ጄምስ ስታየር እንዲህ ይላሉ፦ “እውነት የሚመስልና ዘግናኝ የሆነ የዓመፅ ድርጊት [በመገናኛ ብዙኃን] በተደጋጋሚ የሚመለከት ትውልድ፣ ጠበኝነትን ተቀባይነት እንዳለው ነገር አድርጎ የሚያይ ከመሆኑም ሌላ የጭካኔ ድርጊት እምብዛም የማይረብሸውና የርኅራኄ ስሜት የሌለው ይሆናል።”  እርግጥ ነው፣ በቴሌቪዥን አዘውትረው የዓመፅ ድርጊቶችን የሚያዩ አብዛኞቹ ወጣቶች ሲያድጉ ጨካኝ ወንጀለኞች ይሆናሉ ማለት አይደለም። ይሁን እንጂ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን በቁጣ መገንፈል ተቀባይነት ያለው ነገር እንደሆነ ተደርጎ ብዙውን ጊዜ በመዝናኛው ዓለም ስለሚቀርብ የዓመፅ ድርጊቶች የማይዘገንኑት አዲስ ትውልድ ብቅ ብሏል።
ክፉ መናፍስት የሚያሳድሩት ተጽዕኖ
በዛሬው ጊዜ ሰዎች ጎጂ በሆነ መንገድ ቁጣቸውን እንዲገልጹ የሚያደርጋቸው አንድ የማይታይ ኃይል ከበስተጀርባ እንዳለ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። ይህ ኃይል ምንድን ነው? ገና በሰው ዘር ታሪክ መጀመሪያ ላይ አንድ ዓመፀኛ መንፈሳዊ ፍጡር ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ መቃወም ጀመረ። ይህ ክፉ መንፈሳዊ ፍጡር ሰይጣን ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ስሙም በዕብራይስጥ “ተቃዋሚ” ወይም “ጠላት” የሚል ትርጉም አለው። (ዘፍጥረት 3:1-13) ከጊዜ በኋላም ሰይጣን ሌሎች መላእክትን አግባብቶ በዓመፁ እንዲተባበሩት አደረጋቸው።
አጋንንት ወይም ክፉ መናፍስት በመባል የሚታወቁት እነዚያ ዓመፀኛ መላእክት የሚያሳድሩት ተጽዕኖ በምድር አካባቢ እንዲወሰን ተደርጓል። (ራእይ 12:9, 10, 12) በተጨማሪም አጭር ጊዜ እንደቀራቸው ስለሚያውቁ “በታላቅ ቁጣ” ተሞልተዋል። እነዚህን ክፉ መናፍስት በዓይናችን ልናያቸው ባንችልም የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ መመልከት እንችላለን። እንዴት?  ሰይጣንና አጋንንታዊ ጭፍሮቹ ኃጢአት የመሥራት ዝንባሌያችንን ተጠቅመው እንደ “ጠላትነት፣ ጠብ፣ ቅናት፣ በቁጣ መገንፈል፣ የከረረ ጭቅጭቅ፣ መከፋፈል፣ . . . ምቀኝነት” ባሉትና እነዚህን በመሳሰሉት ነገሮች እንድንካፈል ሊፈትኑን ይሞክራሉ። ገላትያ 5:19-21
በእርግጥም ከላይ ያየናቸውን ችግሮች፣ ተጽዕኖዎችና ውጥረት የሚፈጥሩ ሁኔታዎች ከግምት ካስገባን ሰዎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቻቸውን በሚያከናውኑበት ጊዜ ብስጩ የሚሆኑት ለምን እንደሆነ መረዳት አያዳግተንም።
ጓደኛ ሊሆኑ የሚችሉ ሰዎችን መፈለግ
አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “ከጠቢብ ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የተላሎች ባልንጀራ ግን ጉዳት ያገኘዋል” በማለት ሐቁን አስቀምጦታል። (ምሳሌ 13:20) ብዙ ሰዎች ጓደኛ ሲመርጡ የሚያዩት መግባባታቸውን ብቻ ነው። ከምንግባባቸው ሰዎች ጋር አብረን ስንሆን ደስ እንደሚለን የታወቀ ነው። ሆኖም ስለ እውነተኛ ማንነታቸው ብዙም ትኩረት ሳንሰጥ ስለተግባባን ብቻ ሰዎችን ጓደኛ አድርገን የምንመርጥ ከሆነ ከባድ ችግር ላይ ልንወድቅ እንችላለን። አንድ ሰው ጥሩ ሥነ ምግባር እንዳለውና እንደሌለው እንዴት ማወቅ ትችላለህ?
በቅድሚያ እኛ ራሳችን ጥሩ ሥነ ምግባር ያለን ሰዎች መሆን አለብን። ትክክልና ስህተት የሆነውን፣ ጥሩውንና መጥፎውን ለይተን ማወቅና በማንኛውም ጊዜ ሥነ ምግባራዊ አቋማችንን ጠብቀን መኖር ያስፈልገናል። ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “ብረት ብረትን እንደሚስል፣ ሰውም ሌላውን ሰው እንደዚሁ ይስለዋል” በማለት ይገልጻል። (ምሳሌ 27:17) እንደ ብረት የጠነከረ የሥነ ምግባር አቋም ያላቸው ሁለት ሰዎች ጓደኛሞች ከሆኑ መልካም ባሕርያትን በማዳበር ረገድ እርስ በርስ የሚረዳዱ ከመሆኑም በላይ በመካከላቸው ያለው ወዳጅነት ይበልጥ ይጠናከራል።
 “እኔ እውነተኛ ጓደኛ የምለው በጥሞና የሚያዳምጠኝንና በደግነት የሚያነጋግረኝን እንዲሁም ሳጠፋ የሚገሥጸኝን ሰው ነው” በማለት አስተያየቱን አንድ ስው ሰጥቷል። አዎ፣ የልብ ጓደኞቻችን ወጣትም ሆኑ አረጋዊ ትክክለኛውን አቅጣጫ ይዘን እንድንጓዝ የሚረዱንና ተገቢ ያልሆነ ነገር ልናደርግ ስንል የሚያርሙን መሆን አለባቸው። መጽሐፍ ቅዱስ “የወዳጅ ማቁሰል ይታመናል” በማለት ይገልጻል። (ምሳሌ 27:6) ሥነ ምግባራዊም ሆነ መንፈሳዊ አቋማችንን ለማጠናከር ለአምላክና ለመሠረታዊ ሥርዓቶቹ ፍቅር ካላቸው ሰዎች ጋር ጓደኛ መሆን ይኖርብናል።
ከአንድ ከተዋወቅከው ሰው ጋር ጓደኝነት መመሥረት ከፈለግህ ‘ጓደኞቹ እነማን ናቸው?’ ብለህ መጠየቅህ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። የቅርብ ጓደኞቹ እነማን እንደሆኑ ማወቅህ ስለ እሱ ማንነት ጥሩ ግንዛቤ እንድታገኝ ሊረዳህ ይችላል። በተጨማሪም በአካባቢው ያሉ የጎለመሱና የተከበሩ ሰዎች ለእርሱ ያላቸው አመለካከት ምንድን ነው? እንዲሁም ጓደኛ ልናደርጋቸው ያሰብናቸው ሰዎች ከእኛ ጋር ያላቸው ግንኙነት ጥሩ ስለመሆኑ ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ጋር ስላላቸው ግንኙነት ጭምር ማሰብ ይኖርብናል። በተለይ ከጥቅም አንጻር ብዙም ሊያደርጉላቸው ለማይችሉ ሰዎች ያላቸው አመለካከት ምን ይመስላል? አንድ ሰው በማንኛውም ጊዜ፣ ለሁሉም ሰው እንደ ሐቀኝነት፣ ታማኝነት፣ ትዕግሥትና አሳቢነት የመሳሰሉ ግሩም ባሕርያትን የማያሳይ ከሆነ ለአንተስ ወደፊት ጥሩ ጓደኛ ሊሆንህ እንደሚችል ምን ዋስትና ይኖርሃል?
አንድ ሰው በዕለት ተዕለት ሕይወቱ የሚያንጸባርቀውን እውነተኛ ባሕርይ በደንብ ለማወቅ ትዕግሥትና ብልሃት እንዲሁም ጊዜ ይጠይቃል። መጽሐፍ ቅዱስ “የሰው ልብ ሐሳብ እንደ ጥልቅ ውሃ ነው፤ አስተዋይ ሰው ግን ከዚያ ቀድቶ ያወጣዋል” ይላል። (ምሳሌ 20:5) ጓደኛ ልናደርጋቸው ያሰብናቸውን ሰዎች እውነተኛ ባሕርይ፣ ዝንባሌ እንዲሁም የሥነ ምግባር አቋም መገምገም እንዲያስችለን አንዳንድ ወሳኝ የሆኑ ርዕሰ ጉዳዮችን ማንሳቱ ጥሩ ሊሆን ይችላል። ምን ዓይነት አመለካከት ያላቸው ሰዎች ናቸው? ደግ ናቸው ወይስ አይደሉም? እንዲያው በአብዛኛው ሲታዩ አዎንታዊና ብሩህ አመለካከት ያላቸው ናቸው ወይስ አፍራሽ አመለካከት ያላቸውና ተጠራጣሪዎች? ለጋስ ናቸው ወይስ ራስ ወዳድ? እምነት የሚጣልባቸው ናቸው ወይስ የማይታመኑ? አንድ ሰው ሌሎችን ለአንተ የሚያማ ከሆነ አንተንስ ለሌሎች እንዳያማ ምን ይከለክለዋል? ኢየሱስ “በልብ ውስጥ የሞላውን አንደበት ይናገረዋል” ሲል ገልጿል። (ማቴዎስ 12:34) ሰዎች የሚናገሩት ነገር ማንነታቸውን ስለሚገልጽ ልብ ብለን ማዳመጥ ይኖርብናል።
አንዳንዶች ጓደኞቻቸው ልክ እንደ እነሱ ዓይነት ምርጫ ሊኖራቸው እንደሚገባ አድርገው ያስባሉ። አንድ ትንሽ ልጅ “እኔ የምወደውን ዓይነት ኬክ የማይወድ ሰው በፍጹም ጓደኛዬ እንዲሆን አልፈልግም” ሲል ተናግሯል። እርግጥ ነው፣ ጓደኛሞች እርስ በርስ ይበልጥ ሊግባቡ የሚችሉት በብዙ ነገር የሚመሳሰሉ ከሆነ ነው። በተለይ ደግሞ ተመሳሳይ የሆነ ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ አቋም ሊኖራቸው ይገባል። ይህ ሲባል ግን ባሕርያቸውም ሆነ አስተዳደጋቸው አንድ ዓይነት መሆን አለበት ማለት አይደለም። እንዲያውም የተለያየ የሕይወት ተሞክሮ ያላቸው መሆኑ ሊጠቅማቸውና ጓደኝነታቸውን ሊያጠነክርላቸው ይችላል።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘው በዮናታንና በዳዊት እንዲሁም በሩትና በኑኃሚን መካከል የነበረው ግንኙነት ጓደኝነትን በተመለከተ ጊዜ የማይሽረው ምሳሌ ይሆነናል። እነዚህ ሰዎች የሚያመልኩት አምላክም ሆነ የሚመሩበት መሠረታዊ ሥርዓት አንድ ነበር። በዮናታንና በዳዊት እንዲሁም በሩትና በኑኃሚን መካከል በዕድሜም ሆነ በአስተዳደግ ረገድ ትልቅ ልዩነት ነበር። በመሆኑም ጓደኝነትን በተመለከተ ከእነሱ አንድ ቁምነገር እንማራለን። ይኸውም ወጣቶችና በዕድሜ ትልቅ የሆኑ ጓደኝነት ከመሠረቱ አንዳቸው ከሌላው ጥቅም ማግኘታቸው የማይቀር ነው።
በዕድሜ የተለያዩ መሆን ያለው ጥቅም
ከእኛ በዕድሜ ከሚበልጡ ወይም ከሚያንሱ ጋር ጓደኝነት መመሥረታችን ለሁለታችንም ከፍተኛ ጥቅም ይኖረዋል። በዚህ ረገድ ጥቅም ያገኙ ወጣቶች የተናገሩትን ተሞክሮ እስቲ እንመልከት።
“በዕድሜ ጠና ያሉ አንድ ባልና ሚስት ጓደኞች ነበሩኝ። እኔ የሚሰማኝን ሁሉ እነግራቸዋለሁ፤ ደስ የሚለው ደግሞ እነሱም የሚሰማቸውን ሁሉ ይነግሩኛል። ልጅ ነች ብለው አይንቁኝም። ይህም ይበልጥ እንድወዳቸው አደረገኝ። ከእነርሱ ጋር ጓደኛ መሆኔ በተለይ ችግር ሲገጥመኝ በእጅጉ ጠቅሞኛል። ችግሬን ለዕድሜ እኩዮቼ ሳጫውታቸው ብዙውን ጊዜ የሚሰጡኝ ምክር ያልታሰበበት እንደሆነ አስተውያለሁ። እነዚህ በዕድሜ ጠና ያሉ ጓደኞቼ ግን እኛ ወጣቶች ገና ያልደረስንበት ተሞክሮ፣ ማስተዋልና ብስለት አላቸው። እነዚህ ጓደኞቼ በሕይወቴ ውስጥ ጥሩ ውሳኔዎችን እንዳደርግ ረድተውኛል።”
“ተሰባስበን በምንጫወትበት ጊዜ ወጣቶችን ብቻ ሳይሆን በዕድሜ ጠና ያሉትንም እንጨምራለን። ወጣቶችና አዋቂዎች አንድ ላይ ተሰባስበን ስንጫወት ውለን ማታ ስንለያይ ሁላችንም ተበረታተን ወደ ቤታችን እንደምንመለስ አስተውያለሁ። እንዲህ ያለ አስደሳች ጊዜ እንድናሳልፍ የሚረዳን ሁላችንም በመጠኑም ቢሆን የተለያየ ዓይነት አመለካከት ያለን መሆኑ ነው።”
እናንተ ትልልቆችም ብትሆኑ ወጣቶችን ልትቀርቧቸው ይገባል። ከላይ የተሰጡት አስተያየቶች እንደሚያሳዩት ወጣቶች የእናንተን የካበተ ተሞክሮ የሚያደንቁ ከመሆኑም በላይ አብረዋችሁ መሆን ያስደስታቸዋል። በሰማንያዎቹ ዕድሜ የሚገኙ አንዲት መበለት “ወጣቶችን ሆነ ብዬ እቀርባቸዋለሁ። የእነሱን ብርታትና ጥንካሬ ሳይ እኔም መንፈሴ ይታደሳል!” በማለት ገልጸዋል። በዚህ መንገድ እርስ በርስ መበረታታት ይህ ነው የማይባል ጥቅም አለው። ብዙ ጎልማሶች በሕይወታቸው ደስተኛና ስኬታማ ሊሆኑ የቻሉት ወጣት በነበሩበት ጊዜ በዕድሜ የሚበልጧቸውና ምሳሌ የሚሆኗቸው ጓደኞቻቸው በሰጧቸው ጥሩ ምክር እንደሆነ ይናገራሉ።
ጓደኝነትን ማጠናከር
ጥሩ ጓደኝነት ለመመሥረት አዲስ ጓደኞችን ማፍራት አለብህ ማለት አይደለም። መልካም ባሕርይ ያላቸው ጓደኞች ካሉህ ጓደኝነታችሁ ይበልጥ የሚጠናከርበትን መንገድ ለምን አትፈልግም? የረጅም ጊዜ ጓደኞች ምንጊዜም ውድ ስለሆኑ በአክብሮት ልንይዛቸው ይገባል። በጓደኝነት ያሳለፋችሁትን ጊዜ አቅልለህ ልትመለከተው አይገባም። ከሁሉም በላይ ደግሞ እውነተኛ ደስታም ሆነ እውነተኛ ጓደኛ ማግኘት የምትችለው ራስህን፣ ጊዜህንና ጥሪትህን በመስጠት መሆኑን አትዘንጋ። የምታገኘው በረከት ከምትከፍለው መሥዋዕትነት በእጅጉ የላቀ ነው። ጓደኛ በምትመርጥበት ጊዜ ሁሌ የራስህን ጥቅም ብቻ የምታስብ ከሆነ መቼም ቢሆን ሊሳካልህ አይችልም። በመሆኑም ጓደኛ ለመምረጥ ስታስብ በምታደንቃቸው ወይም ይጠቅሙኛል ብለህ በምታስባቸው ላይ ብቻ አታተኩር። ከዚህ ይልቅ ሌሎች ብዙ ትኩረት የማይሰጧቸውን ወይም ጓደኛ በመመሥረት ረገድ ችግር ያለባቸውን መፈለግ ትችላለህ። ወጣት “እርስ በርስ ተገናኝተን ለመጫወት ስናስብ ብቸኝነት የሚሰማቸው ወጣቶች እንዳሉ ስለምናውቅ እነሱንም እንጋብዛቸዋለን። ‘ብቻህን ቤት ቁጭ ከምትል ከእኛ ጋር መጫወት ትችላለህ፤ በዚያውም እርስ በርስ እንተዋወቃለን’ እንላቸዋለን” በማለት ተናግራለች ። ሉቃስ 14:12-14
በሌላ በኩል ደግሞ ጥሩ ሰዎች ጓደኛ ሊያደርጉህ ሲሞክሩ ቶሎ ብለህ ፊት አትንሳቸው። “ከዚህ ቀደም ሰዎች እንዳገለሉህ ሲሰማህ በውስጥህ ትንሽ ቅሬታ ያድርብሃል። እንዲያውም ‘ጓደኛ ኖረኝ አልኖረኝ ምንም ጥቅም የለውም’ ብለህ ማሰብ ትጀምራለህ። ከዚያም ዝምተኛ ወደመሆን፣ ራስህን ወደማግለልና ስለ ራስህ ብቻ ወደማሰብ ታዘነብላለህ። ጓደኛ ከመፈለግ ይልቅ ሌሎች እንዳይቀርቡህ መንገዱን ሁሉ ትዘጋለህ” በማለት አስተያየቷን ሰጥታለች። አጉል ፍርሃት ወይም ራስ ወዳድነት አዳዲስ ጓደኞች እንዳታፈራ እንቅፋት እንዲሆንብህ ከመፍቀድ ይልቅ ሌሎች እንዲቀርቡህ መንገዱን ክፍት አድርግ። ሌሎች ለአንተ አስበው ጓደኛ ሊያደርጉህ ሲፈልጉ ከልብ ልታደንቃቸው ይገባል።
እውነተኛ ጓደኞች ማፍራት
እውነተኛ ጓደኞችን ለማፍራት ምኞት፣ ሌሎች ለጓደኝነት እስኪጋብዙን ድረስ መጠበቅና ጓደኛ ስለማፍራት ምክር የሚሰጡ ይህን የመሳሰሉ ርዕሶችን ማንበብ ብቻ አይበቃም። ጓደኛ ለማፍራት መሞከር ብስክሌት ለመንዳት ከመለማመድ ጋር ይመሳሰላል። እንዲሁ በማንበብ ብቻ ጓደኛ የማፍራትም ሆነ ብስክሌት የመንዳት ችሎታ ማዳበር አይቻልም። በተደጋጋሚ ልንወድቅ ብንችልም የግድ እየነዳን መለማመድ ያስፈልገናል። መጽሐፍ ቅዱስ ከሌሎች ጋር የጠበቀ ጓደኝነት መመሥረት የምንችለው ከአምላክ ጋር የጸና ወዳጅነት መመሥረት ስንችል እንደሆነ ይናገራል። ሆኖም አምላክ ከእሱ ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት ጥረት የማናደርግ ከሆነ ከሌሎች ሰዎች ጋር ጓደኝነት ለመመሥረት የምናደርገውን ጥረት አይባርክልንም። በእርግጥ እውነተኛ ጓደኞችን ማፍራት ትፈልጋለህ? ከሆነ ተስፋ አትቁረጥ! አምላክ እንዲረዳህ ጸልይ፣ ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ ስሜት ሌሎችን ቅረብ እንዲሁም አንተ ራስህ ጓደኛ ሁን። የእነዚህን ሰዎች ጓደኝነት በተመለከተ ሩት፣ አንደኛ ሳሙኤል እና ሁለተኛ ሳሙኤል የተባሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ማንበብ ትችላለህ።
ለወላጆች የተሰጠ ማሳሰቢያ
 ሌሎች ብዙ ነገሮችን ከቤት እንደምንማር ሁሉ ስለ ጓደኝነትም መማር የምንጀምረው ከቤት ነው። በመሠረቱ የቤተሰብ ሕይወት ራሱ የአንድን ትንሽ ልጅ የጓደኝነት ፍላጎት በሙሉ ያሟላል። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ሥር እያለም እንኳ አንድ ልጅ ከቤተሰቡ ውጭ የሚኖረው ግንኙነት በአስተሳሰቡ፣ በስሜቱና በባሕርይው ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። ለምሳሌ ያህል፣ ከሌላ አገር ተሰደው የመጡ ሕፃናት ልጆች ከሌሎች ልጆች ጋር ባላቸው ግንኙነት ብቻ አንድን አዲስ ቋንቋ ወዲያው የመናገር ችሎታ እንደሚያዳብሩ አስተውለህ ይሆናል።
 ወላጅ እንደመሆንህ መጠን ልጆችህ ጓደኞችን እንዴት በጥበብ መምረጥ እንዳለባቸው የመርዳት ጥሩ አጋጣሚ አለህ። ትንንሽ ልጆችና በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ያለወላጅ እርዳታ ጓደኞቻቸውን በጥበብ ሊመርጡ አይችሉም። ሆኖም በዚህ ረገድ ችግር አለ። አብዛኞቹ ወጣቶች ከወላጆቻቸው ወይም በዕድሜ ከሚበልጧቸው ጋር ከመወዳጀት ይልቅ ከእኩዮቻቸው ጋር መቀራረብን ይመርጣሉ።
ወጣቶች ምክር ለማግኘት ከወላጆቻቸው ይልቅ ወደ እኩዮቻቸው ዞር የሚሉበት አንዱ ምክንያት ወላጆች የወላጅነት ግዴታቸውን በአግባቡ ስለማይወጡ መሆኑን አንዳንድ ባለሙያዎች ተናግረዋል። ወላጆች ለልጆቻቸው መመሪያ ለመስጠት ጥረት በማድረግና ስለ ልጆቻቸው ከልብ የሚያስቡ በመሆን አምላክ የሰጣቸውን ኃላፊነት መወጣት ይጠበቅባቸዋል። (ኤፌሶን 6:1-4) ግን እንዴት? ዶክተር ሮን ታፍል የተባሉ የቤተሰብ ኑሮ አማካሪ በጉርምስና ዕድሜ ላይ ከሚገኙ ልጆቻቸው ጋር እንዴት መግባባት እንደሚችሉ ግራ የገባቸው ብዙ ወላጆች እንደሚያጋጥሟቸው ተናግረዋል። አብዛኞቹ ወላጆች የወላጅነት ግዴታቸውን ከመወጣት ይልቅ “በመገናኛ ብዙኃን በስፋት በሚሰራጨው ዘመን አመጣሽ የልጅ አስተዳደግ ይሸነፋሉ” ብለው ጽፈዋል። ወላጆች ግን በዚህ አመለካከት የሚሸነፉት ለምንድን ነው? “ልጆቻቸውን በደንብ ካለማወቃቸው የተነሳ የእነሱን ሐሳብ መረዳትም ሆነ ለጥያቄዎቻቸው መልስ መስጠት ስለማይችሉ ነው።”
 ሆኖም ወላጆች ከወጣት ልጆቻቸው ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖራቸው ማድረግ ይችላሉ። ልጆች የሚፈልጉትን ነገር ከወላጅ ካላገኙ ወደ ጓደኞቻቸው ዞር ማለታቸው እንደማይቀር ወላጆች ማወቅ አለባቸው። ታዲያ ልጆች የሚፈልጉት ነገር ምንድን ነው?  “ማንኛውም ወጣት የሚፈልገውን ሁሉ ይፈልጋሉ፤ ይህም ማለት እንክብካቤ፣ አድናቆት፣ አይዞህ መባል፣ የማያሻማ መመሪያ፣ ከእነሱ ምን እንደሚጠበቅ ግልጽ የሆነ ማብራሪያና በቤተሰቡ ውስጥ ተፈላጊ እንደሆኑ የሚያረጋግጥ ነገር ይፈልጋሉ” በማለት ተናግረዋል። አክለውም “የሚያሳዝነው ግን በዛሬው ጊዜ ያሉ አብዛኞቹ ወጣቶች ወላጆቻቸው ከላይ የተዘረዘሩትን ፍላጎቶቻቸውን ሊያሟሉላቸው አልቻሉም፤ እንዲሁም ቤተሰባቸው ‘የራሳቸው ቤተሰብ እንደሆነ’ አይሰማቸውም” ብለዋል።
ልጆቻችሁ ጥሩ ጓደኞች እንዲያፈሩ እንዴት መርዳት ትችላላችሁ? በመጀመሪያ ደረጃ አንተ ራስህ ሕይወትህን የምትመራበትን መንገድና የጓደኛ ምርጫህን በተመለከተ በጥሞና አስብ። የአንተም ሆነ የጓደኞችህ አኗኗርና የሕይወት ግብ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነና በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው? መንፈሳዊ ነው ወይስ በቁሳዊ ነገሮች ላይ ያተኮረ? “ከቃልህ ይልቅ ድርጊትህ ተጽዕኖ ስለሚያሳድር ልጆችህ የአንተንም ሆነ የጓደኞችህን እንዲሁም የጓደኞችህን ልጆች ጠባይና ድርጊት እንደሚያስተውሉ መዘንጋት የለብህም”
 እንስሳት እንኳን በደመ ነፍስ በመመራት ልጆቻቸውን ከአደጋ ለመጠበቅ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። ስለ ድብ የሚያጠኑ አንድ ባለሙያ እንዳሉት “እናት ድቦች ግልገሎቻቸውን ሊያጠቃ ከሚችል ከማንኛውም ነገር በመከላከል ረገድ የታወቁ ናቸው” በማለት ተናግረዋል። ታዲያ ሰብዓዊ ወላጆችስ ከዚህ ያነሰ ነገር ማድረግ ይጠበቅባቸዋል?  ወጣት “ወላጆቼ ከአጉል ጓደኛ ጋር ስገጥም ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ እያወጡ በማስረዳት ይመክሩኝ ነበር። በዚህ ጊዜ መጀመሪያ የሚሰማኝ ስሜት ‘ተመልከቱ እንግዲህ! ጭራሽ ጓደኞች መያዝ አልችልም ማለት ነው እኮ’ የሚል ነበር። ጊዜ እያለፈ በሄደ ቁጥር ግን ወላጆቼ ትክክል መሆናቸውን መገንዘብ ችያለሁ፤ ለትዕግሥታቸው አመሰግናቸዋለሁ፤ ከክፉ እንድጠበቅ ረድተውኛል” በማለት ተናግሯል።
በተጨማሪም ልጆቻችሁን ከሌሎች ማለትም መልካም ምሳሌ ከሚሆኑና ጥሩ ግቦችን ለማውጣት ከሚረዷቸው ጓደኞች ጋር እንዲተዋወቁ አድርጉ። ደስተኛና ጥሩ ደረጃ ላይ የሚገኝ ወጣት “እናታችን ወንዶቹ ልጆች ማንኛውንም ነገር የምናደርገው በአብዛኛው እርስ በርሳችን እንደሆነ ስላስተዋለች በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ ያሉ ወጣት ወንድሞችን ቤት ትጋብዝልን ነበር። ይህም ከእነሱ ጋር እንድንተዋወቅና ጓደኝነት እንድንመሠርት ረድቶናል” በማለት እናታቸው ያደረገችላቸውን በማስታወስ ይናገራል። በበኩልህ እንደዚህ የመሰለ ጥረት ካደረግክ ልጆችህ ጥሩ ጓደኝነት ሊመሠርቱ የሚችሉበት አጋጣሚ ልትፈጥርላቸው ትችላለህ።

0 comments:

Post a Comment