- ተራሮች ሳይወለዱ፥ ምድርም ዓለምም ሳይሠሩ፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ አንተ ነህ።
- ትርጉም ያለው ሕይወት መኖር“አንድ ሰው ሀብታም ቢሆንም እንኳ ሕይወቱ በንብረቱ ላይ የተመካ [አይደለም]።” ሉቃስ 12:15በሕይወት ውስጥ ከሚያስፈልጉን ነገሮች አንዱ ሠርቶ ገንዘብ ማግኘት ነው። እግዚአብሄር አምላክ ለራሳችንም ሆነ ለቤተሰባችን የሚያስፈልገውን የማሟላት ኃላፊነት ጥሎብናል።—1 ጢሞቴዎስ 5:8ገንዘብም ሆነ ገንዘብ ሊገዛቸው የሚችላቸው ነገሮች መሠረታዊ ፍላጎትህን ለማሟላት የሚያገለግሉ ከመሆን አልፈው በሕይወትህ ውስጥ ትልቅ ቦታ ቢይዙስ? በሕይወትህ ውስጥ ዋነኛ ዓላማህ ገንዘብ መሰብሰብ ቢሆንስ? ሀብትን ለማካበት ቅድሚያ የሚሰጡ ሰዎች እዚህ ግባቸው ላይ ለመድረስ ሲሉ ማጭበርበር ሌሎችንም እግዚአሄር የማይወዳቸውን ተግባሮች ለማድረግ ይገደዳሉ ወይም ይቀናቸዋል።ብዙ ሰዎች የሚኖሩት ገንዘብንና ገንዘብ የሚገዛቸውን ነገሮች ለማግኘት ሲሉ ነው። አንዳንዶች በዓለም ላይ ታዋቂ ለመሆን ይደክማሉ። ሌሎች ደግሞ በሥነ ጥበብ መስክ ያላቸውን ችሎታ ለማሳደግ ይጥራሉ። ሌሎችን ለመርዳት ሲሉ መላ ሕይወታቸውን የሰጡም አልታጡም። ይሁንና አብዛኞቹ ሰዎች ለመድረስ የሚጣጣሩበት ግብ የሌላቸው ከመሆኑም ሌላ የሕይወት ዓላማ ምን እንደሆነም አያውቁም።መጽሐፍ ቅዱስ በመክብብ 7:12 ላይ “ገንዘብ ጥላ ከለላ እንደ ሆነ ሁሉ፣ ጥበብም ጥላ ከለላ ነው፤ የዕውቀት ብልጫዋ ግን፣ ጥበብ የባለቤቷን ሕይወት መጠበቋ ነው” ይላል። አዎን፣ ገንዘብ ጥቅም አለው። ገንዘብ ለኑሮ፣ በተለይም ደግሞ ቤተሰብ የምታስተዳድር ከሆነ ኃላፊነትህን ለመወጣት ያስፈልግሃል። 1 ጢሞቴዎስ 5:8። ገንዘብ በሚገዛቸው ነገሮች መደሰት እንችላለን።ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን የሚያስጠጋበት ቦታ እንደሌለው የተናገረ ማቴዎስ 8:20፤ ዮሐንስ 2:1-11፤ 19:23, 24። ኢየሱስ በሕይወቱ ውስጥ ቅድሚያ የሰጠው ደስታን ለማሳደድ አልነበረም። ኢየሱስ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ነገሮች ነበሩት። ኢየሱስ ‘የሰው ሕይወቱ በሀብቱ ብዛት ላይ የተመሠረተ እንዳልሆነ’ ተናግሯል። አክሎም፣ እርሻው ፍሬያማ ስለሆነለትና እንደሚከተለው ሲል ስላሰበ አንድ ባለጠጋ የሚገልጽ ምሳሌ ተናገረ:- “ምርቴን የማከማችበት ስፍራ ስለሌለኝ ምን ላድርግ? . . . ያሉኝን ጐተራዎች አፈርስና ሌሎች ሰፋ ያሉ ጐተራዎች እሠራለሁ፤ በዚያም ምርቴንና ንብረቴንም ሁሉ አከማቻለሁ፤ ነፍሴንም፣ ‘ነፍሴ ሆይ፤ ለብዙ ዘመን የሚበቃሽ ሀብት አከማችቼልሻለሁ፤ እንግዲህ ዕረፊ፤ ብዪ፤ ጠጪ፤ ደስም ይበልሽ’ እላታለሁ።” የዚህ ሰው አስተሳሰብ ስህተቱ ምን ላይ ነበር? ምሳሌው በመቀጠል “እግዚአብሔር ግን፣ [ሀብታሙን ሰው] አንተ ሞኝ፤ ነፍስህን በዚህች ሌሊት ከአንተ ሊወስዱ ይፈልጓታል፤ እንግዲህ፣ ለራስህ ያከማቸኸው ለማን ይሆናል? አለው” ይላል። ሰውየው ምርቱን ቢያከማችም እንኳ ከሞተ ያካበተው ሀብት የሚፈይድለት ነገር የለም። ኢየሱስ ምሳሌውን ሲደመድም “ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ዘንድ ሀብታም ያልሆነ ሰው መጨረሻው ይኸው ነው” በማለት ለአድማጮቹ ግሩም ትምህርት ሰጣቸው። ሉቃስ 12:13-21። እርግጥ ነው፣ የተወሰነ ገንዘብ ያስፈልገናል፤ መዝናኛም ቢሆን የራሱ ቦታ አለው። ይሁን እንጂ ገንዘብም ሆነ ተድላ በሕይወታችን ውስጥ ትልቁን ቦታ የሚይዙ ነገሮች አይደሉም። በሕይወታችን ውስጥ ቅድሚያ ልንሰጠው የሚገባው ነገር በአምላክ ዘንድ ሀብታም መሆንን ማለትም በእሱ ዘንድ ሞገስ የሚያስገኝ ኑሮ መምራትን ነው።በርካታ ሰዎች ስመ ጥር ለመሆን ሲደክሙ ይታያሉ። በሌሎች ዘንድ ጥሩ ስም ለማትረፍ መፈለግ ሙሉ በሙሉ ስህተት ነው ለማለት አይቻልም። መጽሐፍ ቅዱስ “መልካም ስም ከመልካም ሽቱ ይበልጣል፤ ከልደትም ቀን የሞት ቀን ይሻላል” ይላል። መክብብ 7:1አንድ ሰው በሚሞትበት ጊዜ፣ ያሳለፈው የሕይወት ተሞክሮ በሙሉ በመዝገብ ላይ ተጽፏል ለማለት ይቻላል። አንድ ሰው በሕይወቱ ውስጥ መልካም ነገሮችን አድርጎ ከነበረ የሞተበት ቀን፣ ይህ ነው ተብሎ ሊነገርለት የማይችል የሕይወት ታሪክ ካልነበረበት ከተወለደበት ቀን እጅግ የተሻለ ነው።የመክብብ መጽሐፍን የጻፈው ንጉሥ ሰሎሞን ነው። የሰሎሞን ታላቅ ወንድም የነበረው አቤሴሎም ስሙን ማስጠራት ይፈልግ ነበር። ይሁንና በመጪው ትውልድ ስሙን ሊያስጠሩለት የሚችሉት ሦስት ወንዶች ልጆቹ ገና በልጅነታቸው የሞቱበት ይመስላል። ታዲያ አቤሴሎም ምን አደረገ? መጽሐፍ ቅዱስ “አቤሴሎም፣ ‘ስሜን የሚያስጠራ ልጅ የለኝም’ በማለት መታሰቢያ እንዲሆነው በሕይወት እያለ የንጉሥ ሸለቆ በተባለው ስፍራ በራሱ ስም ሐውልት አቁሞ” እንደነበር ይገልጻል። (2 ሳሙኤል 14:27፤ 18:18) በዛሬው ጊዜ ይህ ሐውልት በስፍራው ላይ አይገኝም። አቤሴሎምም ቢሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ዘንድ የሚታወቀው የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ለመቀማት ያሴረ የወጣለት ዓመጸኛ በመሆኑ ነው።በዛሬው ጊዜ፣ በርካታ ሰዎች ባከናወኑት ነገር ለመታወስ ይጥራሉ። ፍላጎታቸው እንደየወቅቱ በሚቀያየረው በሰው ልጆች ፊት ክብር ለማግኘት ይደክማሉ። ይሁንና የእንዲህ ዓይነቱ ዝና መጨረሻ ምንድን ነው? ክሪስቶፈር ላሽ ዘ ካልቸር ኦቭ ናርሲሲዝም (ከልክ በላይ ራስ ወዳድ የመሆን ባሕል) በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንደሚከተለው ሲሉ ጽፈዋል:- “የአንድ ሰው ስኬት በአብዛኛው የሚለካው ወጣት መስሎ በመታየቱ፣ በውበቱና አዲስ ነገር በመሥራቱ በሆነበት በአሁኑ ወቅት ዝነኝነት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ወዲያው የሚያልፍ ነገር ሆኗል። የብዙሃኑን ቀልብ ለመሳብ የበቁ ሰዎችም ቢሆን ዝናቸውን እንዳያጡ ሁልጊዜ ይሰጋሉ።” ከዚህም የተነሳ ብዙዎቹ ታዋቂ አርቲስቶች ወደ አደንዛዥ ዕፅና ወደ አልኮል መጠጥ ዞር ስለሚሉ የአብዛኞቹ ሕይወት በአጭሩ ይቀጫል። በእርግጥም ዝነኛ ለመሆን መድከም ከንቱ ነው።ታዲያ ጥሩ ስም ማትረፍ ያለብን በማን ዘንድ ነው? እግዚአብሄር ሕጉን ስለጠበቁ አንዳንድ ሰዎች በኢሳይያስ በኩል ሲናገር “በቤተ መቅደሴና በቅጥሮቼ ውስጥ፣ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች የበለጠ፣ መታሰቢያና ስም እሰጣቸዋለሁ፤ ለዘላለም፣ የማይጠፋ ስም እሰጣቸዋለሁ” ብሏል። (ኢሳይያስ 56:4, 5) ለእግዚአብሄር ታዛዥ በመሆናቸው ምክንያት በእሱ ዘንድ ሞገስ ያገኙ ሰዎች “መታሰቢያና ስም” ይሰጣቸዋል። እግዚአብሄር ስማቸውን “ለዘላለም” ስለሚያስታውስ አይጠፉም። መጽሐፍ ቅዱስ የሚያበረታታን እንዲህ ዓይነቱን ማለትም በፈጣሪያችን ፊት መልካም የሆነ ስም እንድናተርፍ ነው።ኢሳይያስ ታማኝ የሆኑ ሰዎች የዘላለም ሕይወት ስለሚያገኙበት ጊዜ ተንብዮአል። በዚያች ገነት ውስጥ የሚኖረው “የዘላለም ሕይወት” እግዚአብሄር አምላክ የሰው ልጆችን ሲፈጥራቸው ሊሰጣቸው አስቦት የነበረው ‘እውነተኛ ሕይወት’ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 6:12, 19) ጊዜያዊና እርካታ የሌለው ሕይወት ከመምራት ይልቅ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት መጣጣር አይኖርብንም?ሥነ ጥበብ ወይም በጎ አድራጎት ብቻውን አርኪ ሕይወት አያስገኝም :- በርካታ አርቲስቶች በያዙት የሥነ ጥበብ ዘርፍ አንከን የለሽ ነው ብለው ወደሚያስቡት የሥራ ውጤት ለመድረስ ሲሉ ሥራቸውን እያሻሻሉ ለመሄድ ብርቱ ፍላጎት አላቸው። ሕይወት ደግሞ ይህን ለማድረግ በጣም አጭር ነው። አንድ አርቲስት በሥራው ለመርካት በሚችልበት ደረጃ ላይ ቢደርስም እንኳ ወጣትና ጤነኛ በነበረበት ጊዜ ያደርገው እንደነበረው ሁሉ ብዙ የጥበብ ሥራዎችን መሥራት አይችል ይሆናል። ይሁንና ለዘላለም መኖር ቢችል ኖሮስ? የጥበብ ሥራውን ምን ያህል እንከን የለሽ አድርጎ ሊሠራው እንደሚችል አስብ!ሕይወትን ለበጎ አድራጎት ሥራ ስለመስጠትስ ምን ለማለት ይቻላል? አንድ ሰው ለድሆች ትኩረት መስጠቱና ጥሪቱን በችግር ላይ ያሉትን ለመርዳት ማዋሉ የሚያስመሰግነው ነው። መጽሐፍ ቅዱስም “የሚሰጥ ብፁዕ [“ደስተኛ፣”] ነው” ይላል። (የሐዋርያት ሥራ 20:35) በእርግጥም ለሌሎች ደህንነት ማሰብ እርካታን ያስገኛል። ይሁን እንጂ አንድ ሰው ለዚህ ሥራ መላ ሕይወቱን ቢሰጥ እንኳ ምን ያህል ለውጥ ማምጣት ይችላል? እኛ ሰዎች የሌሎችን ችግር ለመፍታት ልናደርግ የምንችለው ነገር በጣም ውስን ነው። የትኛውንም ያህል ከፍተኛ ቁሳዊ እርዳታ ቢደረግ ብዙዎች ችላ የሚሉትን እጅግ መሠረታዊ የሆነውን የሰው ልጆች ፍላጎት ማሟላት አይቻልም። ሰዎች ደግሞ ይህ ፍላጎት ካልተሟላላቸው መቼም ቢሆን እርካታ ሊያገኙ አይችሉም።ኢየሱስ በተራራው ስብከቱ ላይ ይህን መሠረታዊ የሆነ ተፈጥሯዊ ፍላጎት አስመልክቶ ሲናገር “በመንፈሳዊ ድኾች መሆናቸውን የሚያውቁ ደስተኞች ናቸው። መንግሥተ ሰማያት የእነሱ ነውና” ብሏል። (ማቴዎስ 5:3) በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው እውነተኛ ደስታ ሀብትንና ዝናን በማግኘት፣ በሥነ ጥበብ ዘርፍ ስኬታማ በመሆን ወይም ለሌሎች በጎ በማድረግ ላይ የተመካ አይደለም። ከዚህ ይልቅ መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ማለትም አምላክን ለማምለክ ያለንን ውስጣዊ ስሜት በማርካት ላይ የተመካ ነው።ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ፈጣሪን የማያውቁ ሰዎች እግዚአብሄርን እንዲፈልጉት ሲያበረታታቸው እንዲህ ብሏል:- “[እግዚአብሄር] የሰውን ዘር ሁሉ ከአንድ ወገን ፈጥሮ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ አደረገ፤ የዘመናቸውን ልክና የመኖሪያ ስፍራቸውንም ዳርቻ ወሰነላቸው። ይኸውም ሰዎች እግዚአብሔርን ፈልገው ተመራምረው ምናልባት ያገኙት እንደ ሆነ ብሎ ነው፤ ይህም ቢሆን እርሱ ከእያንዳንዳችን የራቀ ሆኖ አይደለም፤ የምንኖረውና የምንቀሳቀሰው፣ ያለነውም በእርሱ ነውና።” የሐዋርያት ሥራ 17:26-28በሕይወት ውስጥ እውነተኛ ደስታ ለማግኘት ቁልፉ እውነተኛውን አምላክ ለማምለክ ያለንን ፍላጎት ማርካት ነው። መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ማርካታችን ‘የእውነተኛ ሕይወት’ ተስፋ ያስገኝልናል። ለምሳሌ ያህል፣ ራሷ በምታዘጋጀው አንድ ሰዓት በሚፈጅ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ላይ የመጀመሪያዋ ጥቁር አሜሪካዊ የፊልም ተዋናይ በመሆን በአገሯ ታዋቂነት ያተረፈችውን የአንድ ጥቁር አሜሪካዊ የተዋናይ ታሪክ እንመልከት። ይህቺ ዘነኛ ተዋናይ ብዙም ሳትቆይ ሁሉንም ነገር እርግፍ አድርጋ ተወችው። ይህን ያደረገችው “የእግዚአብሄር ቃል የሚሰጠውን ምክር መስማት የተሻለ ሕይወት ለመምራት የሚያስችል መሆኑን ስላመንኩበት ነው” ብላለች። ይህች ተዋናይ የጾታ ብልግናንና ዓመጽን የሚያበረታታ የቴሌቪዥን ድራማ ላይ በመተወን ከአምላኳ ጋር ያላትን ወዳጅነት ማበላሸት አልፈለገችም። ተዋናይዋ በሌሎች ፊት እንደ ኮከብ እንድትታይ ያደረጋትን ሥራ መሥራቷን ያቆመች ብትሆንም የእግዚአብሄር መንግሥት ምሥራች የሙሉ ጊዜ ሰባኪ በመሆንና ሌሎች ከእግዚአብሄር ከአምላክ ጋር ጥሩ ወዳጅነት እንዲመሠርቱ በመርዳት እውነተኛ እርካታ በሚያስገኝላት የሕይወት ጎዳና ላይ መጓዝ ጀመረች።የቀድሞ የሥራ ባልደረባዋ የነበረ አንድ ሰው የትወና ሥራዋን ለማቆም ያደረገችውን ውሳኔ አስመልክቶ እንዲህ የሚል አስተያየት ሰጥቶ ነበር:- “ስኬታማ ሆናበታለች ብዬ ያሰብኩትን ሥራ እንደ ዋዛ ስትተወው ስመለከት እጅግ አዘንኩ። ይሁን እንጂ የተሻለ ነገር እንዳገኘች ግልጽ ነው።” ቆየት ብሎ፣ ተዋናይዋ ሕይወቷን አጣች። ከሞች በኋላ፣ ይህ የቀድሞ የሥራ ባልደረባዋ እንዲህ ብሏል:- “ደስተኛ ነበረች። ሰው በሕይወቱ የሚፈልገው ደግሞ ይህንኑ ነው። ደስተኞች ነን ብለን መናገር የምችለው ስንቶቻችን ነን?” በሕይወታቸው ውስጥ ከእግዚአብሄር ጋር ላላቸው ወዳጅነት ቅድሚያ ሲሰጡ ኖረው በሞት ያንቀላፉ ሰዎች የእግዚአብሄር መንግሥት በሚገዛበት ወቅት ትንሣኤ የማግኘት አስደናቂ ተስፋ አላቸው። ዮሐንስ 5:28, 29።ፈጣሪ ለምድርም ሆነ በውስጧ ለሚኖሩት የሰው ልጆች ዓላማ አለው። አንተም ይህን ዓላማ እንድትረዳና የዘላለም ሕይወት እንድታገኝ ይፈልጋል። (መዝሙር 37:10, 11, 29) የሰማይና የምድር ፈጣሪ ስለሆነው ስለ እግዚአብሄር ለመማርም ሆነ አምላክ ለአንተ ያለውን ዓላማ ለማወቅ ጊዜው አሁን ነው።
0 comments:
Post a Comment